በዮናታን ሙሉጌታ እና አምሀ ተስፋዬ
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ በሁለተኛ የምድብ ጨዋታዎች ሲቀጥል ኢትዮጵያ ቡና ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፉን ያረጋገጠበትን ድል፤ መከላከያ ደግሞ የመጀመርያ 3 ነጥቡን አስመዝግቧል።
09:00 ላይ በመከላከያ እና አዳማ ከተማ መካከል የተከናወነው ጨዋታ በመከላከያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የጀመረው ይህ ጨዋታ በመከላከያ የአማካይ ክፍል የበላይነት ቀጥሎ አዳማን ከሜዳው እምብዛም እንዳይወጣ አድርጎታል። በዚህ መልኩ በአጫጭር ቅብብሎች በተደጋጋሚ ወደ አዳማ ሳጥን ይገቡ የነበሩት መከላከያዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከግማሽ ጨረቃው አካባቢ መቶ ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ ሆነዋል።
ከምንይሉ ጎል በኋላ ግን ተነቃቅተው የታዩት አዳማዎች ነበሩ። ከተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር ጀርባ በመግባትም የተሻለ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተው 23ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ቡልቻ ሹራ ከይድነቃቸው ጋር አንድ ለአንድ በተገናኘበት ቅፅበት ግብ ጠባቂው ጥፋት ሰርቶበት አዳማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት ደስታ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ቡልቻ ሹራም በደረሰበት ጉዳት በብዙዓየው እንዳሻው ተቀይሮ ወጥቷል። በቀሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎችም አዳማዎች በፍጥነት ከጎሉ ርቆ በሚታውየው የጦሩን የተከላካይ መስመርን በማለፍ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ቡድኑ በሙሉቀን እና በቡዛየው ያደረጋቸው ሙከራዎችም ኢላማቸውን ጠብቀው በይድነቃቸው ጥረት የዳኑ ነበሩ። በተለይም ሙሉቀን ከአዲሱ ተስፋዬ ቀምቶ ያደረገው ሙከራ ለግብ በእጅጉ የቀረበ ነበር። ደቂቃዎቹ ሲገፉ የአዳማን አማካይ ክፍል አልፎ መግባት የተሳናቸው መከላከያዎችም ከቴዎድሮስ ታፈሰ በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር የሞከሩ ሲሆን ተመስገን ገ/ኪዳን እና ፍሬው ሰለሞን ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሻሉ ነበሩ።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ቀዝቀዝ ያለ ነበር። ቡድኖቹ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የማይደርሱበት በመሆኑም መሀል ሜዳ ላይ የሚታዩ ፍትጊያዎች የተበራከቱበት ሆኖ ዘልቋል። በፍጥነት ሰብሮ ከተከላካይ መስመር ጀርባ የመግባት ብቃታቸው የቀነሰው አዳማዎች በረከት ደስታን ባማከሉ እንቅስቃሴዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም እንደ ዱላ ሙላቱ ያሉ የመስመር አጥቂዎችን በማስገባት ጭምር በግራ እና በቀኝ ለመግባት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። መከላከያዎችም ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢኖራቸውም ሙከራዎቻቸው ግን በቁጥር ጥቂት ነበሩ። ምንይሉ ወንድሙ ከግቡ ግራ እና ቀኝ የሚያገኛቸው እና ወደላይ የሚልካቸው ኳሶች ተደጋግመው የታዩ ሲሆን አጥቂው 70ኛው ደቂቃ ላይ ከሳሙኤል ታዬ ተቀብሎ አክርሮ ሞክሮት ጃፋር ደሊል ያወጣው በተሻለ መልኩ ለጎል የቀረበበት አጋጣሚ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ቅፅበት ፍሬው ሰለሞንን ቀይሮ የገባው አቤል ከበደ በግንባሩ ወደ ግብ የላካት ኳስ ጃፋርን አልፋ ከመግባቷ በፊት ቴዎድሮስ በቀለ ሊያድነት ቢጥርም ሳይሳካለት መከላከያን 2-1 እንዲያሸንፍ ረድታለች። በውጤቱም አዳማ ከተማ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋው ሲመናመን በተቃራኒው መከላከያ ዕድሉን አስፍቶበታል።
የአዳማ ከተማው የመስመር አጥቂ በረከት ደስታ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።
11:20 ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ በቡና 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ተቀዛቅዞ በተጀመረው ጨዋታ በ12ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ በወጣበት ኳስ የኤሌክትሪክን የተከላካይ መስመር መፈተሽ የጀመሩት ቡናዎች በቃልኪዳን ዘላለም አማካኝነት በ17 ኛው እና 21 ኛው ደቂቃ ሙከራዎች ቢያደርግም በግብ ጠባቂው ዮሐንስ በዛብህ ጥረት ሊከሽፉ ችለዋል። በ25ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ቶማስ ስምረቱ ሳይጠቀምበት ሲቀር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ኢትዮጽያ ቡና ከአምስቱ ጎሎች ቀዳሚውን አግኝቷል። በ27ኛው ደቂቃ አዲስ ፈራሚው አጥቂ ሉካዋ ኒስምባ እየገፋ በመግባት ያመቻቸለትን ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቃልኪዳን ዘላለም ወደግብነት በመለወጥ ቡናን መሪ አድርጎል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ኤሌክትሪኮች ኳስ በመቆጣጠር ወደፊት ለመጠጋት ጥረት ቢያደርጉም የጠራ የግብ እድል በመፍጠር ረገድ ደክመው ታይተዋል። በዚህም በ41ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ነጋሽ ከቅጣት ምት የሞከረውና በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ከወጣበት ሙከራ ውጪ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበት ተጨማሪ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡናዎች የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረው ሲቀርቡ ኤሌክትሪኮች በመክፈቻው ከመከላከያ ጋር እንዳደረጉት ጨዋታ ሁሉ በዛሬው ጨዋታም በአካል ብቃት ረገድ ተዳክመው በመግባት የቡናን ጥቃት ለመመከት ሲቸገሩ አምሽተዋል። ለቡና ጥሩ የማጥቃት አማራጭ መሆኑን እያሳየ የሚገኘው ኮንጓዊው ሱሌይማን ሎክዋ በ53ኚው ደቂቃ አስራት ቱንጆ ሲመታ ተጨርፎ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት በመለወጥ የቡናን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ኤሌክትሪኮች ግቡ ሊፀድቅ አይገባም በሚል በዳኛው ላይ ተቃውሞ ቢያሰሙም ግቡ ፀድቆ ጨዋታው ቀጥሏል።
ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቡናዎች ተቀይረው ወደ ሜዳ በገቡ ወጣት ተጫዋቾች አማካኝነት በተከታታይ በተቆጠሩ ጎሎች ልዩነቱን ማስፋት ችለዋል። በ64ኛው ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን ሲያስቆጥር በ75ኛው ደቂቃ በኤሌክትሪክ ተከላካዮች ስህተት የተገኘውን አጋጣሚ የኃላሸት ፍቃዱ ወደ ግብነት ለውጦታል። በተጨማሪው ደቂቃ ደግሞ ተመስገን ዘውዱ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በመምታት የማሳረጊያዋን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በውድድሩ ኢትዮጵያ ቡናን በአምበልነት እየመራ የሚገኘው አማካዩ ሳምሶን ጥላሁን የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።
የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታዎችን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ6 ነጥቦች ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፉን ሲያረጋግጥ መከላከያ በ3 ነጥቦች እና ያለምንም ጎል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ኤሌክትሪክ በ3 ነጥቦች እና በአራት የግብ እዳ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዳማ ከተማ ያለምንም ነጥብ መጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የነገ (ሐሙስ) ጨዋታዎች
ጅማ አባ ጅፋር ከ ወላይታ ድቻ – 09፡00
ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ – 11፡00