የቀድሞው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በአራት ዓመት ውስጥ ከፍሎ ያላጠናቀቀው ውዝፍ እዳን ከፍሎ ለመጨረስ በግንቦት ወር የተመረጠው አዲሱ የፌዴሬሽን አመራር የመንግስትን ድጋፍ ሊጠይቅ መሆኑ ታውቋል።
ያለፉትን አራት ዓመታት (ከ2006-2010) በአቶ ጁነይዲ ባሻ እየተመራ እግርኳሱን በበላይነት ይመራ የነበረው አመራር በቆይታው በተለያዩ ምክንያቶች ለክለቦች ፣ ለሆቴሎች እና ተያያዥ ለተቋማት ከፍሎ ያላጠናቀቀው ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ውዝፍ እዳ እንዳለበት እየተነገረ ይገኛል።
ፌዴሬሽኑ ለክለቦች የስታድየም ገቢ ድርሻቸውን ለመክፈል ሲቸገርና ክለቦችም “ድርሻችን ካልተከፈለ አንጫወትም” እስከማለት የደረሰ ቅሬታ ሲገልፁ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን በቅርቡ በተደረገው የ2010 የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ሪፖርት እና የ2011 ዕጣ ማውጣት መርሐ ግብር ላይ ከተመልካች ገቢ ለክለቦች ያልተከፈለ የሁለት ዓመት12 ሚሊዮን ብር እዳ እንዳለበት መገለፁ ይታወሳል። “ከዚህ ዓመት ጀምሮ አንድ ጨዋታ በተደረገ በሦስተኛው ቀን ገንዘቡ በክለቦቹ አካውንት እንዲገባ እናደርጋለን ” በማለት ም/ፕሬዝደንቱ ኮ/ል አወል አብዱራሒም መናገራቸውም ይታወቃል።
የዚህ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እዳ በምን ምክንያት ነው የተፈጠረው የሚለውን ዝርዝር ጉዳይ በግልፅ የተቀመጠ ባለመሆኑ አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራር ግልፅ የሆነ ማብራሪያ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ለመምራት የተመረጠው አዲሱ የፌዴሬሽን አመራር ትኩረቱን በእግርኳስ ልማት ላይ ከማድረግ ይልቅ እዳዎቹን በመክፈል ላይ እንዲጠመድ የሚያደርገው ሲሆን ከመንግስት፣ ከተለያዩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ሀገራት ድጋፍ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል።