በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከምድብ ሀ ለግማሽ ፍፃሜው ያለፉ ቡድኖች ታውቀዋል

ዛሬ በተደረጉ የአዲስ አበባ ዋንጫ ምድብ ሀ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ ለግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡባቸው ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ዛሬ የተደረጉት ሁለቱ የምድብ ሀ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው አስቀድሞ ከትናንት በስትያ ከዚህ ዓለም በሞት ያጣነው አሰልጣኝ ሥዩም አባተ በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የታሰበ ሲሆን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላከው የሀዘን መግለጫም ተነቧል።

08፡15 ሲል የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታቸውን የጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ በመፈራረቅ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን እየወሰዱ በዘለቁበት የመጀመሪያው አጋማሽ አዳማዎች በሱራፌል ጌታቸው ፣ ቡዛየው እንዳሻው እና ሙሉቀን ታሪኩ አማካይነት ቀድመው ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ኳስ ከመያዙ ባለፈ የተሻለ የግብ ዕድልን ሊፈጥሩ የሚችሉ ኳሶችን ወደ ፊት በማድረሱም በኩል አዳማዎች ተሽለው ታይተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በአጫጭር ቅብብሎች የተጋጣሚያቸውን የመሀል ክፍል አልፈው ለመሄድ ቢሞክሩም በጥቂት አጋጣሚዎች ነበር እስከሳጥኑ ድረስ መዝለቅ የቻሉት ፤ ከነዚህ ውስጥም የ19ኛው ደቂቃ የአቤል አክሊሉ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የሚጠቀስ ነው። ሆኖም የአዳማው አዲስ አጥቂ ብዙአየው እንዳሻው 27ኛ ደቂቃ ላይ ከኦኛ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ካመከነው ኳስ በሰከንዶች ልዩነት ከቀኝ መስመር የተነሳው አዲሳለም ደሳለኝ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። 


ከአዲሳለም ግብ በኋላ ግን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ነበሩ ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉት። በተለይም ከቡድኑ የቀኝ ጎን ይነሱ የነበሩ ኳሶች ይበልጥ አስፈሪ ሆነው ሲታዩ 31ኛው ደቂቃ ላይ በዛው ቦታ የተሰለፈው አብበከር ደሳለኝ ያደረገው ሙከራ በዳንኤል ተሽመ ጥረት የዳነ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ባይሆንላቸውም በሀይሉ ተሻገር እና ተክሉ ተስፋዬም ሌሎች ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር።


ከእረፍት መልስ ሁለት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አቻ ሆነዋል። ከቀኝ አቅጣጫ የተላከለትን ኳስ ተከትሎ የገባው አቤል አክሊሉ በፈጠረው አጋጣጣሚ ተክሉ ተስፋዬ ግቧን ማስቆጠር ችሏል። ተክሉ 51ኛው ደቂቃ ላይም ሌላ ኳስ ከርቀት በቀጥታ በመምታት ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ጨዋታው ድራማዊ አጋጣሚን አስተናግዷል። በዚህም 54ኛው ደቂቃ ላይ ብዙአየው እንዳሻው በተስፋዬ ሽብሩ ተጠልፎ አዳማዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ምኞት ደበበ አስቆጥሮ በድጋሜ መሪ አደረጋቸው። ሆኖም ከደቂቃ በኃላ በሌላኛው ፅንፍ ቴዎድሮስ በቀለ ቢኒያም ትዕዛዙን በመጥለፉ ኤሌክትሪኮችም ተነሳሳይ ፍርድ ተሰጥቷቸው አዲስ ነጋሽ ቡድኑን በፍፁም ቅጣት ምት አቻ አድርጓል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በብዛት ኳስ ተቆጣጥረው እና ከባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የተሻለ የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ አሳይተው በዘለቁበት የጨዋታ ሂደት አዳማዎችን እምብዛም ከሜዳቸው እንዳይወጡ አድርገዋል። ቢሆንም የፈጠሯቸውን የግብ ዕድሎች ባለመጠቃማቸው የነበራቸው የጨዋታ ብልጫ በውጤት የታጀበ እንዳይሆን አድርጎታል። አዳማዎችም ከብዙአየሁ የርቀት ሙከራዎች ውጪ ያለቀለት የግብ ዕድል ያገኙት በ90ኛው ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ ከቀኝ መስመር በላከው ኳስ ቢሆንም ከኦኛ ጋር ፊት ለፊት የመገናኘት አጋጣሚ ያገኘው አዲስ ህንፃ ኳሷን መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ጨዋታው በ 2-2 ውጤት ተጠናቋል። 


የኢትዮ ኤሌክትሪኩ በሀይሉ ተሻገር የጨዋታው ኮከብ ሆኖ በመመረጥ ከቀድሞው የኢትዮ ኤሌክትሩክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች አንዋር ሲራጅ እጅ ሽልማቱን ተረክቧል።



10፡35 ላይ የምድቡ የመጨረሻው እና አላፊዎችን የለየው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ መካከል ተደርጓል። ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡናዎች ፈጣን ማጥቃት የጀመረ ቢሆንም መከላከያዎች 3ኛው ደቂቃ ላይ ነበር መሪ መሆን የቻሉት። መሀል ሜዳ ላይ ቶማስ ስምረቱ ሚዛኑን በመሳቱ ያለፈችውን ኳስ ተመስገን ገ/ኪዳን እየነዳ ገብቶ አሳልፎለት ምንይሉ ወንድሙ ጎሏን ማስቆጠር ችሏል። 



በቀጣዮቹም ደቂቃዎች መከላከያዎች ሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመያዝ እና ለኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ቀርበው በማጥቃትም ጭምር የበላይነቱን የወሰዱበት ነበር ፤ ሆኖም የነበራቸው የበላይነት በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። እንደ የመጨረሻ ሙከራም 27ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ታዬ ከፍሬው ሰለሞን ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ብቻ ነው ሊነሳ የሚችለው። በሂደት በተጨዋቾች የሜዳ ላይ ግጭት ውጥረት እየነገሰበት በመጣው በዚህ ጨዋታ ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች የበላይነቱ ከተጋጣሚያቸው መውሰድ ችለዋል። በተደጋጋሚ የተጨዋቾች የግል ስህተት ሲታይባቸው የነበሩት እና በአንድ ለአንድ ግንኙነትም ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ቡናዎች እንደ መከላከያ ሁሉ ጥሩ በተንቀሳቀሱባቸው ደቂቃዎች በርካታ የመጨረሻ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም። 34ኛው ደቂቃ ላይ ከዳንኤል ደምሴ በተነሳ ኳስ ሉኩዋ ሱለይማን ይድነቃቸውን አልፎ የሞከረው እና ወደ ላይ የተነሳው ኳስ አንደኛው የቡድኑ ሙከራ ሲሆን ሉኩዋ ሱለይማን  እና ዳንኤል ደምሴ ያደረጓቸው ሌሎች ሁለት ሙከራዎችም በተመሳሳይ ኢላማቸው ሳይጠብቁ የቀሩ ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ፈጣን የሆኑና እና ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተቃራኒያቸው የግብ ክልል የደረሱባቸውን እንቅስቃሴዎች አስመልክቶናል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከዳዊት ማሞ በደረሰው ኳስ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዋቴንጋ ኢስማ እና የግቡ አግዳሚ የመለሱበት አጋጣሚ ደግሞ አስደንጋጩ ሙከራ ነበር። ከደቂቃዎች በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ምላሹን ለመስጠት በጦሩ ሳጥን ውስጥ በተገኙበት ቅፅበት አበበ ጥላሁን አበበከር ነስሩን በመጎተቱ የፍፁም ቅጣት አግኝተዋል። ነገር ግን ሉኩዋ ሱለይማን ፍፁም ቅጣት ምቱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አጋጣሚው ካመለጣቸው በኋላም ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቡናዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ቢሆንም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ አሁንም ንፁህ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ተስኗቸዋል። 67ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ድምሴ በግንባሩ ሞክሮት ይድነቃቸው ያዳነበት ሙከራም የተሻለ ተብሎ የሚነሳ ነበር። የተጋጣሚያቸውን ጥቃት እምብዛም ሳይቸገሩ ማርገብ የቻሉት መከላከያዎችም 85ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ማሞ ከፍሬው ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ከሞከረበት አጋጣሚ ውጪ የጠራ የግብ ዕድል አላገኙም። ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በጥቅሉ ሲታይ የፉክክር ግለቱ የጨመረበት እና በርካታ ቢጫ ካርዶች የተመዘዙበት ሆኖ ተገባዷል።



በተመዘገበውም ውጤት ኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ በእኩል ስድስት ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከምድባቸው ማለፋቸው እርግጥ ሆኗል። የመከላከያው የአማካይ መስመር ተሰላፊ ፍሬው ሰለሞን ደግሞ የጨዋታው ኮከብ በመሆን መመረጥ ችሏል።