በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ምድብ ስድስት የምትገኘው ኢትዮጵያ የምድቡን 4ኛ ጨዋታ በናይሮቢ ካሳራኒ ስታድየም አከናውና 3-0 በሆነ ውጤት በመሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሏን አጨልማለች።
ከ4 ቀናት በፊት ባህር ዳር ላይ ተገናኝተው ያለ ግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በስታድየም የተገኘውን ቁጥር የተመለከተው የኬንያ መንግስት ተመልካቾች የዛሬውን ጨዋታ በነጻ ገብተው እንዲከታተሉ በመወሰኑ ምክንያት የካሳራኒ ስታድየምም በተመልካች ተሞልቶ ተካሂዷል።
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ከባህር ዳሩ ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ በማድረግ በቢንያም በላይ ምትክ ሽመክት ጉግሳን በማካተት ጨዋታውን ሲጀምሩ የኬንያው ሴባስቲየን ሚኜ የሁለት ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።
በኬንያዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጀመረው ጨዋታ የሀራምቤ ከዋክብት በኢትዮጵያ ላይ ያሳደሩት ጫና የተከላካይ መስመሩ እንዳይረጋጋ እና ቅርፁ እንዲበታተን አድርጎታል። በ8ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው በረጅሙ የተለጋውን ኳስ የዋልያዎቹ ተከላካዮች በአግባቡ ባለማራቃቸው ኤሪክ ኦውማ አግኝቶ በመምታት ወደ ውጪ የወጣበት ኳስም የተከላካይ ክፍሉን መጋለጥ ያሳየ አጋጣሚ ነበር።
ጨዋታው ቀጥሎ በ23ኛው ደቂቃ ዮሀና ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል የነበረው ሚኬል ኦሉንጋ በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት ማራኪ ጎል አስቆጥሮ ኬንያን ቀዳሚ አድርጓል። ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከግራ መስመር ኤሪክ ኦውማ ያሻገረውን ኳስ የኢትዮጵያ ተከላካዮች በአግባቡ ባለማራቃቸው ሳጥኑ ጠርዝ ላይ የነበረው ዮሀና ኦሞንድ በጠንካራ ምት ወደ ጎልነት ለውጦ የጎል ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ከኬንያ የመሪነት ጎሎች በኋላ ቀሪው የመጀመርያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ የሚጠቀስ ሙከራ አልታየበትም። ይልቁንም ጥፋቶች እና የማስጠንቀቂያ ካርዶች በርክተውበታል። ያልተደራጀው እና በጎሎቹ መቆጠር ይበልጥ ቅርፁን ያጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በጨዋታው የግብ እድል ለመፍጠርም ሆነ የኬንያዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ የሚያስችል እንቅስቃሴ ሳያደርግ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሻሽሎ ይቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም በዚህ አጋማሽም ያሳየው ከመጀመርያው የተለየ አልነበረም። በተለይም የተከላካይ መስመሩ በተደጋጋሚ የሚሰራቸው ስህተቶች ለኬንያ ሁነኛ የጎል እድል ሲፈጥርላቸው ታይቷል። ተሻጋሪ ኳሶች የሚያርቁበት መንገድ ደካማ መሆን እና የአማካዮቹ ለተከላካዮች ተገቢውን ሽፋን አለመስጠት የሚመለሱ ኳሶችን የኬንያ ተጫዋቾች በቀላሉ እንዲያገኙና የጎል እድል እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል። በ50ኛው ደቂቃ ሚኬል ኦሉንጋ ከአንተነህ ተስፋዬ የቀማውን ኳስ ወደ ፊት ገፍቶ ግብ ጠባቂው ሳምሶንን ቢያልፈውም አንተነህ ደርሶ ወደ ውጪ ያወጣበት ኳስ የቡድናችንን አለመረጋጋት ያሳየ ነበር። በ65ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ዮሀና ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲገባ በአህመድ ረሺድ ጥፋት ተሰርቶበት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት የሃራምቤ ከዋክብቶቹ አምበል ሲክቶር ዋኒያማ አስቆጥሮ የቡድኑንም መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ሶስተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የዋሊያዎቹ አለቃ አብርሃም መብራቱ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በአንፃራዊነት በተሻለ ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል። በአካላዊ ግዝፈቱ ለዋሊያዎቹ ተከላካዬች ፈተና መሆኑን የቀጠለው ሚካኤል ኦሉንጋ በ73ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ወደ መሃል እየገፋ ሄዶ የሞከረው ኳስ ሌላ ግብ ለመሆን ቀርቦ የመከነ አጋጣሚ ሲሆን የፊት መስመር አጥቂው ጌታነህ ከበደ በ78ኛው ደቂቃ ወደ ኋላ በመመለስ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ በመምታት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርጓል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ዳዋን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ኡመድ ከጋቶች የደረሰውን ኳስ ከርቀት ወደ ግብ ሞክሮ ኳሱ ሃይል ስላልነበረው እና ኢላማዋውን በመሳቱ በቀላሉ ወደ ውጪ ወጥቷል።
በጥሩ ሽግግሮች ሲጫወቱ የነበሩት ኬንያዎች ከዚህች ሙከራ በኋላ ጫናቸውን ቀነስ አድርገው ተጫውተዋል። ባለሜዳዎቹ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ለማጥቃት የራሳቸውን ሜዳ ለቀው ሲወጡ በሚያገኙት ክፍተት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር በመንቀሳቀስ በ87ኛው ደቂቃ አንተነህ ተስፋዬን ቀምተው ያገኙትን ግልፅ የግብ ማግባት እድል ዴኒስ ኦዲያምቦ ሞክሮ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቷል። ዋሊያዎቹ ከጨዋታው ማስተዛዘኛ ጎል ለማግኘት በስተመጨረሻ በሙሉ ሃይላቸው ያጠቁ ሲሆን ተጋጣሚያቸው በአንፃሩ ክፍተቶችን ተጠቅመው ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር በሚካኤል ኦሉንጋ አማካኝነት ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውም በኬንያ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱ ኬንያን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ ተስፋን ሲያሰንቅ በሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን ያስተናገደውና በአብርሀም መብራቱ አሰልጣኝነት ዘመን የመጀመርያ ሽንፈት ያስመዘገበው ብሔራዊ ቡድናችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋው መንምኗል።