የሊጉ ቻምፒዮኖች ወሳኙን የመሀል ተከላካያቸውን አቆይተዋል።
የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ዘንድሮ በብዙው የተለውጠ ቡድን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ምክንያት የሆነው በቡድኑ አስደናቂ ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበራቸው ተጨዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች የማምራታቸው ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ከአምናው ቡድን ውስጥ ክለቡን ሳይለቁ የቆዩ ተጫዋቾች መኖራቸውም መዘንጋት አይኖርበትም። ከነዚህ ጥቂት ተጨዋቾች መካከል ደግሞ አዳማ ሲሶኮ አንዱ ነው።
ማሊያዊው ኢንተርናሽናል አምና የጅማ አባ ጅፋርን የተከላካይ ክፍል በመምራት በግሉ ወጥ እና ጠንካራ አቋም ማሳየት ችሏል። ከኤልያስ አታሮ ፣ ቢኒያም ሲራጅ እና መላኩ ወልዴ ጋር በተለያዩ ጊዜያት የፈጠረው የመሀል ተከላካይ ክፍል ጥምረትም የተዋጣለት ሆኖ ጅማ አባ ጅፋር ጥቂት ግቦች ያስተናገደ የሊጉ ክለብ በመሆን ዋንጫውን እንዲያነሳ ወሳኝ ሚናን ተወጥቷል። ይህን አገልግሎቱን በመመልከትም ክለቡ በአዲሱ የውድድር ዓመት ማሊያዊውን በጅማ ለማቆየት ከስምምነት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ፊርማውን ሳያኖር ቆይቷል። ሆኖም አሁን እንደ ሌላው የቡድን አጋሩ ዳንኤል አጄዬ ሁሉ ግዙፉ የመሀል ተከላካይ በይፋ ውሉን አራዝሞ በክለቡ እንደሚቆይ እርግጥ ሆኗል።