በሴቶች እግር ኳስ ውስጥ ከሚጠቀሱ ጠንካራ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ ባለፈው የውድድር ዓመት ያሳየውን ደካማ ውጤት ለማሻሻል ያለመ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድን ውል ሲያድስ አስር አዳዲስ ተጫዋቾችንም አስፈርሟል።
በክለቡ ረጅም ጊዜ የቆየው አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በክለቡ ውስጥ ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል። ዮሴፍ ሀዋሳ ከተማ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ በተከታታይ ዓመታት ንግድ ባንክ እና ደደቢትን ተከትሎ የሶስተኛ ደረጃን እንዲሁም 2009 ደደቢትን በመርታት የጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን እንዲሆንም ያስቻለ አሰልጣኝ ነው ፡፡
ከአሰልጣኙ የኮንትራት ዕድሳት በኃላ ክለቡ ልምድ ያላቸውን እና ከፕሮጀክቶች በድምሩ 10 ተጫዋቾች አምጥቷል። ከሁለት አመት በፊት ሀዋሳ ከተማን ለቃ ወደ አዳማ ከተማ አምርታ የነበረችው አማካይዋ መቅደስ ማሞን ጨምሮ ርብቃ ጣሳው ( ተከላካይ ከንግድ ባንክ) ፣ ምህረት ተስፋዓምላክ (ተከላካይ ከአዳማ) ፣ መቅደስ ተሾመ (የመስመር አጥቂ ከጌዲኦ ዲላ) ፣ ፍሬህይወት በድሉ (አማካይ ከቅ/ማርያም) ፣ ወርቅነሽ መሠለ (አማካይ ከአቃቂ ቃሊቲ) ፣ ዝናቧ ቡጤ (አማካይ ከአርባምንጭ) ፣ ዓይናለም ወንድሙ እና ማዕረግነሽ ማቲዮስ ( ከዱራሜ ፕሮጀክት) ፣ እሙሽ ዳንኤል (ከሲዳማ ፕሮጀክት) የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው። ከሊግ ክለቦች የመጡት ተጫዋቾች የአንድ እና የሁለት ዓመታት ውል ሲሰጣቸው ከፕሮጀክት የመጡት ደግሞ በሦስት ዓመት ውል ነው ክለቡን የተቀላቀሉት።
ሀዋሳ ከአዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ የተጫዋቾችን ውል። በማደስ ላይም ይገኛል። ተከላካዮቹ አረጋሽ ፀጋ እና ፀሀይ ውላቸው ሲታደስ በቀጣይ ቀናት ደግሞ ከታዳጊ ቡድኑ ተጫዋቾች እንደሚያሳድግ እና የ2009 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራን ከንግድ ባንክ መልሶ ለማስፈረም መቃረቡን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡