ሽረ እንዳሥላሴ ናይጄርያዊ ግብ ጠባቂ አስፈረመ

ሽረ እንዳሥላሴ ላለፉት ሁለት ሳምንታት የሙከራ እድል ሰጥቶት የነበረው ናይጄርያዊ ግብጠባቂ ሰንደይ ሮቴሚ በተሰጠው የሙከራ ግዜ ክለቡን ማሳመኑ ተከትሎ ክለቡ በቋሚነት እንዳስፈረመው ለማወቅ ተችሏል።

በትግራይ ክልል ዋንጫ ምርጥ ብቃታቸው ካሳዩ ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው ይህ የ38 ዓመት አንጋፋ ግብ ጠባቂ ከዚህ በፊት የእስራኤሉ ክለብ ሃፖል አሽከሎን እና የሀገሩ ክለብ ሰንሻይን ስታርስን ጨምሮ ለስምንት ክለቦች የተጫወተ ልምድ ያለው ግብ ጠባቂ ነው።

ሃገሩ ናይጄርያን ወክሎ አራት ጨዋታዎች ተሰልፎ የተጫወተው ይህ ግዙፍ ግብ ጠባቂ በ2011 በሳምሶን ሲያስያ በሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት ከኢትዮጵያ ጋር 2-2 በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ነበር።

ሮቴሚ ባለፈው የውድድር ዓመት ክረምት ወደገጅማ አባ ጅፋር በመምጣት ጥሩ የሙከራ ጊዜ አሳልፎ ክለቡ የማስፈረም ፍላጎት አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ያልተጠናቀቀ ውል የነበረው በመሆኑ ጅማ የናይጄርያዊውን ግብ ጠባቂ ዝውውር በመተው ዳንኤል አጄይን ማስፈረሙ የሚታወስ ነው።