ሶከር ሜዲካል| ኳስን በተደጋጋሚ በግንባር መግጨት የአንጎል ጉዳትን ያስከትላል?

የህክምናና የጤና ጉዳዮችን ከእግር ኳስ ጋር አቆራኝተን በምንመለከትበት የሶከር ሜዲካል አምዳችን ብዙውን ጊዜ ጥያቄ የሚነሳበትን ኳስን በግንባር መግጨት ሊኖረው ስለሚችለው ጉዳት እንመለከታለን። ይህ ፅሁፍ በአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተዘጋጀ ሲሆን ወደ አማርኛ በመተርጎም እና ከሀገራችን ነበራዊ ሁኔታዎች ጋር በማስተሳሰር እንደዚህ አቅርበንላችኋል።

ታዋቂው የቀድሞ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ፣ ኒውካስል እና ብላክበርን አጥቂ አለን ሽረር በተጫዋችነት ዘመኑ ኳስን በግንባሩ በመግጨት ይታወቃል ። ሽረር ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ በመናገር ግንዛቤን ለመፍጠር ከሚተጉ ሰዎች መካከልም አንዱ ነው። ጫወታ ካቆመ በኋላ በቴሌቭዥን ተንታኝነት እና አምደኛ በመሆን የሚሰራው ሽረር በተደጋጋሚ ኳስ በመግጨቴ የአንጎል ህመም (Dementia) ይኖርብኝ ይሆን የሚል ፍርሃት እንደነበረበት ገልፆአል።

የነርቭ በሽታዎች ተመራማሪ የሆነው ዊሊ ስትዋርት በእግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር በተገኘ ድጋፍ መሰረት እግር ኳስ ያቆሙ ተጫዋቾች ላይ ምርመራን አድርጓል።

ጄፍ አስትል የተሰኘ እንግሊዛዊ ተጫዋች በ59 አመቱ ያረፈበት ምክንያት chronic traumatic encephalopathy (CTE) እንደሆነ ስትዋርት ገልፀዋል። እንደዚህ አይነቱ በሽታ ብዙውን ጊዜ በቦክሰኞች ላይ የሚስተዋል ነው። ተመራማሪው ሲናገርም በእንደዚህ ባሉ በሽታዎች ላይ የሚደረጉ ጥናቶች በቂ ቁጥራዊ መረጃ እንደሌላቸው እና ለተለያዩ ግምቶች ተጋላጭ እንደሆኑ ገልፀዋል ።

ስቱዋርት እንግሊዝ በ1966 አለም ዋንጫን ባሸነፈችበት ወቅት ተጫዋች የነበሩ ሶስት ሰዎች የመረሳት በሽታ (አልዛይመር) እንዳጋጠማቸው ይናገራል። እነዚህ ተጫዋቾች ማርቲን ፒተርስ (74 አመት) ፣ ሬይ ዊልሰን እና ኖቢ ስታይልስ ናቸው (ሁለቱ ተጫዋቾች ህይወታቸው አልፏል)።

ተመራማሪው ሲቀጥልም ያገጠማቸው ህመም በቀጥታ ከእግር ኳስ ገር መገናኘቱን እና አለመገናኘቱን ማወቅ እንደማይቻል ተናግሯል። መንስኤዎቹን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የሌሎች ሀገራት ተጫዋቾች ላይ ጉዳት መድረስ እና አለመድረስን በእርግጠኝነት ማወቅ እንደሚያስፈልግም አክሎ ተናግሯል።

አንጎል ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች የግድ ኳስን በተደጋጋሚ በግንባር ከመግጨት ጋር የማይዛመድበት ወቅት አለ። ለምሳሌ ያህል እርስ በእርስ በመጋጨት ጭምርም መሰል የጤና እከሎች ያጋጥማሉ።

በአሁኑ ወቅት በእግር ኳስ ሜዳ የሚገኙ ኳሶች እንደ ከዚህ ቀደም በጣም ጠንካራ እና በግንባር ሲገጩ ህመምን የሚያሳድሩ አይደሉም። የአየር ላይ ኳሶች እምብዛም ጥቅም ላይ በማይውሉበት ሊጋችንም የአንጎል ጉዳት ከግጭት የመደርስ እድሉ ኳስ በግንባር ከመምታት ጋር ሲነፃፀር ላቅ ያለ ይመስላል።

እነ ስትዋርት ለጥናታቸው ይረዳ ዘንድ ወደ 20 የሚጠጉ ተማሪዎችን ከሰበሰቡ በኋላ በግንባር ኳሶችን እንዲገጩ አድርገዋቸዋል ። ከዚህ በኋላ የአንጎላቸውን ስርአት ለማጤን ሞክረዋል ። በተገኘውም ውጤት መሰረት የማሰብ እና የማስታወስ አቅማቸው በመጠኑ የመቀነስ አዝማሚያን አሳይቷል ። ይህ ለውጥ የቆየው ግን ለ24 ሰአታት ብቻ ነው። ለረጅም ጊዜ የሚኖረው ጉዳትን ለመግለፅ ግን አስቸጋሪ ሆኗል ።

FIFA እና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በወጣት ተጫዋቾች ላይ ጥናቶች እንዲደረጉ ድጋፍ በመስጠት ላይ ናቸው። ይህም የጉዳዩ አሳሳቢነት ትኩረት እየሳበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ለወደፊትም በርካታ ጥናቶች እንደሚደረጉ እና ተጫዋቾችም ከተለያዩ ጉዳቶች በቂ ከለላ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ።