ጅማ አባጅፋር ያለፉትን ወራት የሙከራ ዕድል ሰጥቶት ከክለቡ ጋር የቆየው ጋናዊው ኢንተርናሽናል ቢስማርክ ኒህይራ አፒያን አስፈርሟል።
አምና የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ጅማ አባ ጅፋር ኦኪኪ አፎላቢን በኮከብ ግብ አግቢንት ማስመረጡ ይታወሳል። የናይጄሪያዊው አጥቂ ያስቆጠራቸው 23 ግቦችም ለክለቡ የቻምፒዎንነት ጉዞ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው የሚታመን ነው። ነገር ግን እንደ አብዛኞቹ ተጨዋቾች ሁሉ ኦኪኪም ከጅማ በመልቀቁ ክለቡ የእሱን ቦታ በአግባቡ የሚሸፍን ተጫዋች እንዲፈልግ አድርጎታል። ክለቡ ኦኪኪ ፊት ላይ ትቶት የሄደውን ይህን ክፍተት ለመሙላትም ጋናዊውን አጥቂ ቢስማሪ አፒያን ለአንድ ወር ያህል የሙከራ ዕድል ከሰጠው በኋላ በመጨረሻም ለአንድ ዓመት በሚቆይ ውል በቋሚነት አስፈርሞታል።
ከ2013 እስከ 2015 በሰቢያው ሶልጋ ፔትሮቫግ ያሳለፈው አጥቂ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ለቦትስዋናው ጋብምሮኒ ዩናይትድ አሳልፏል። በመቀጠልም አጥቂው በድጋሜ ወደ ሰርቢያ በማምራት በ2016/1/7 ለፕሮሌተር ኖቪሳድ እና ባካ ፓላንካ የተጫወተ ሲሆን አምና በሌላኛው የሰርቢያ ሱፐር ሊጋ ክለብ ሞልደስት ሉቻኒ ቆይታ አድርጓል።