የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጀምር ቀናት ቀርተውታል። ሶከር ኢትዮጵያም የክለቦችን የዝግጅት ወቅት እና ቀጣይ መልክ የምታስቃኝባቸውን ፅሁፎች በማቅረብ ላይ ትገኛለች። ለዛሬም ትኩረቷን ኢትዮጵያ ቡና ላይ አድርጋለች።
የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ቡና በ2003 ያጣጣመውን ብቸኛ የፕሪምየር ሊግ ድል ለመድገም በሞከረባቸው ያለፉት ሰባት ዓመታት ተፈላጊውን ውጤት ባያመጣም ዘንድሮም ሁለተኛውን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ወደ ውድድር እንደሚገባ ይታመናል። ክለቡ አምና በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ስር ሆኖ ዓመቱን ይጀምራል ተብሎ ሲጠበቅ ቆይቶ በአዛውንቱ አሰልጣኝ የጤና እክል ምክንያት ፊቱን ወደ ሌላው ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች አዙሮ ነበር። ሆኖም ከአዲሱም አሰልጣኝ ጋር እስከ ከአራተኛው ሳምንታት የዘለለ ጊዜን መቆየት ሳይችል ቀርቶ ፈረንሳዊውን አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስን ከሳምንታት በኋላ ማግኘት ችሏል። አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ በውድድር መሀል ላይ ኃላፊነቱን ከመረከባቸው አንፃር ሲታይ ያስመዘገቡት ውጤት የሚያስከፋ አልነበረም። ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቡድኑ በ50 ነጥቦች ሊጉን ሲያጠናቅቅ ከሻምፒዮኑ በአምስት ነጥቦች ብቻ እርቆ ነበር። ቡና 14 ጨዋታዎችን በማሸነፍ እኩል ስምንት ጊዜ ደግሞ አቻ በመውጣት እና በመሸነፍ 38 ግቦች አስቆጥሮ 22 አስተናግዶ በ16 የግብ ልዩነቶች ነበር የውድድር ዓመቱን የዘጋው።
የ2010 የውድድር ዓመት እንደተገባደደ ክለቦች ወደ ዝውውር ገበያው በሚገቡበት ወቅት ኢትዮጵያ ቡና ከአስራአራት ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል። ውሳኔው ለረጅም ጊዜ በክለቡ ውስጥ የቆዩ ተጫዋቾችንም ጭምር ያካተተ በነሆኑ በቀጣዩ ዓመት ክለቡ ለየት ያለ መልክ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ጥቆማ የሰጠ ነበር። በዚህን መሰረት መስዑድ መሀመድ ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ አስቻለው ግርማ ፣ ኤፍሬም ወንደሰን ፣ ሀሪሰን ሄሱ ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ ፣ ጁቤድ ዑመድ ፣ አስናቀ ሞገስ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ አክሊሉ አያናው ፣ ትዕግስቱ አበራ ፣ ዓለማየሁ ሙለታ ፣ ሮቤል አስራት እና ባፕቴስት ፋዬ ቡናን ለቀዋል። በነዚህ ተጫዋቾች ምትክ ሌሎችን ለማምጣት ውድ በሆነው ዝውውር መስኮት ቀስ በቀስ በመሳተፍ እስካሁን ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል። ስምንቱ ተጫዋቾች ተካልኝ ደጀኔ (ተከላካይ ከአርባምንጭ ከተማ) ፣ ተመስገን ካስትሮ (ተከላካይ ከአርባምንጭ ከተማ) ፣ ዳንኤል ደምሴ (አማካይ ከወልዲያ) ፣ አህመድ ረሺድ (ተከላካይ ከድሬዳዋ ከተማ) ፣ ኢስማኤል ዋቴንጋ (ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ከቫይፐርስ ዩጋንዳ) ፣ የኋላሸት ፍቃዱ (አጥቂ ከገላን ከተማ) ፣ ካሉሻ አልሀሰን (ጋናዊ አማካይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ) እና ሱሌይማን ሎክዋ (ኮንጓዊ አጥቂ ከናፕሳ ስታርስ ዛምቢያ) ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ስር ለወጣት ተጫዋቾች የመሰለፍ ዕድልን እየሰጠ የሚገኘው ቡና ቢኒያም ካሳሁን ፣ እስራኤል መስፍን ፣ ተመስገን ዘውዱ እና ፍፁም ጥላሁንን ወደ ዋናው ቡድኑ አሳድጓል።
አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የክለባቸውን የዝውውር ጊዜ አስመልክተው ሲናገሩ “በዝውውሮች ወቅት 60% ስኬት ማስመዝገብ ከቻልክ ጥሩ የሚባል ጊዜ ነበረህ ማለት ነው። እንደማስበው እስካሁን ያስፈረምናቸው ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ናቸው። አዳዲሶቹ ፈራሚዎች በጣም ጥሩ ነገሮችን ቡድናችን ላይ እንደሚጨምሩ አስባለው። አንድ ጥሩ ፍጥነት እና ክህሎት ያለው ተጨማሪ የመስመር ተጨዋች ከሊቢያ ለማምጣትም ጥረት ላይ ነን። አንድ ተጨማሪ የፊት አጥቂም ያስፈልገናል። አቡበከር እና እያሱ ጉዳታቸው ምን ያህል እንደሚያቆይ እርግጠኛ አይደለንም። ሆኖም ስጋት ላይ የሚጥለን አይሆንም።” ይላሉ። በርግጥም ክለቡ የፈፀማቸው ዝውውሮች እንደሌሎቹ የሀገራችን ክለቦች ሁሉ ቀጥራቸው ከፍ ማለቱ በቂ የቅንጅት ስራ ለመስራት እና አቋማቸውን በአዲሱ ክለባቸው ልክ ለማድረግ ጊዜ እንዲወስድ የሚያደርግ ቢሆንም ከዕድሜ እና ብቃት አንፃር ሲታይ ጥሩ የሚባል ዓይነት ነው። አሰልጣኙም አምና በክሪዝስቶም ንታንቢ ፣ እያሱ ታምሩ እና አማኑኤል ዮሃንስ ላይ ያሳዩንን አይነት የሜዳ ላይ ማንነት በሌሎቹም ላይ በማስረፅ ፈራሚዎቹን በአዲስ ዓይነት ሚና እንድናያቸው ሊያደርጉን ይችላሉ።
ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጣቸው ተመስገን ካስትሮ ፣ አማኑኤል ዮሀንስ እና አህመድ ረሺድ ውጪ ያለውን ስብስብ በመያዝ ከነሀሴ 20 ጀምሮ በባህር ዳር የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅቱን የጀመረው ኢትዮጽያ ቡና መስከረም 13 ለኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ወደ ሀዋሳ አቅንቷል። የውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታው በሽንፈት በመጠናቀቁም መስከረም 16 ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ቃሊቲ በሚገኘው የኒያላ ሜዳ ላይ ዝግጅቱን ቀጥሎ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ስለነበራቸው የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅት አጠቃላይ ሀሳባቸውን ሲናገሩ ” ለአዲሱ የውድድር ዓመት ጠንካራ እና ፈታኝ ሆነን ለመቅረብ የሚረዳንን የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅት አድርገናል ። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ዋንጫ በመከላከያ መሸነፋችን ቢያስከፋኝም በነበረን የዝግጅት ወቅት በጣም ደስተኛ ነኝ። በአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ደግሞ በቡድኔ ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን እየተመለከትኩ ነው። ” ይላሉ። አሰልጣኙ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅታቸው ዋነኛ ትኩረት የአካል ብቃት እንደነበረ ተናግረዋል። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም ” የኔ የጨዋታ ፍልስፍና እና መንገድ ከፍተኛ የአካል ብቃትን ይጠይቃል። በተለይም ከኳስ ውጪ ስንሆን ተጋጣሚዎቻችን ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር እና ብዙ ሳንሮጥ ኳስ መቀማት መቻል ስላለብን በአካል ብቃቱ ዝግጁ መሆን አለብን። ስለሆነም ያለፉትን ስድስት ሳምንታት ብዙ ሰርተናል ። ምንአልባትም በዝቶም ሊሆን ይችላል ለተጨዋቾቹም አድካሚ ነበር። ነገር ግን የሰራነው ስራ ለሚጠብቁን ጊዜያት በሙሉ በጉልበት እንድንጫወት የሚያደርገን ነው። በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥም ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ እንደምንሆን ይሰማኛል አሁንም ጥሩ ዕድገት እየተመለከትኩ ነው። ነገር ግን ከዚህም በላይ መሻሻል እንደምንችል አስባለው። ደግሞም ለውድድር ዝግጁ የሆኑ ተጫዋቾች እንዳሉ ሁሉ በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ካሉሻ እና ሳምሶን ብዙ የሚቀራቸውም አሉ። ስለዚህ በተናጠል የምንሰራቸው ስራዎችም ይኖራሉ። ” ብለዋል።
ክለቡ ከፈፀማቸው ዝውውሮች ባለፈ አምና የተፈጠረውን የአሰልጣኞች መቀያየርን ቀድሞ ለመከላከል የአሰልጣኙን ውል ማራዘሙ በበጎ ጎን የሚነሳ ነው። ለቡድኑ መረጋጋት እና ወጥነትም ይህ ውሳኔ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ይገመታል። አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ በአጨዋወት ደረጃም እንደ አምናው ሁሉ ክለቡ የሚታወቅበትን በቅብብሎች እና በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት እንደሚተገብሩ ይጠበቃል። የፈፀሟቸው ዝውውሮች ደግሞ በየቦታው ላይ ከሚሰጧቸው አማራጮች አንፃር በቡድን አወቃቀራቸው ላይ መጠነኛ ለውጦችን በማድረግ አቀራረባቸውን ለመቀየር ዕድልን ያገኛሉ። ” ቡድኔን በ4-3-3 እንዲጫወት መርጣለው። ነገር ግን በአዲስ አበባ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታችን ላይ 4-4-2 ዳይመንድን ተጠቅመናል ፤ በጥሩ የአጥቂዎች እንቅስቃሴም አመርቂ ነገር አይቼበታለው። እንደ አንድ አማራጭም ልንጠቀምበት የምንችለው ነው። በተጨማሪም አራት እና ሦስት ጥሩ የመሀል ተከላካዮችም ስላሉን በሶስት ተከላካዮች በሚጀምር ፎርሜሽንም የመጠቀም ዕድሉ ይኖረናል። ዋናው ነገር ግን ጨዋታውን መቆጣጠር መቻላችን ላይ ነው። ኳስን ለረጅም ጊዜ የሚቆጣጠር ቡድን ያስፈልገናል። ደግሞም የቡናም የአጨዋወት ባህል እንደዛ ነው። ” የሚለው የፈረንሳያዊው አስተያየት ይህን የሚያጠናክር ነው።
የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የዘንድሮው ዕቅድ ዋንጫ ማንሳት መሆኑን መገመት አይከብድም። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ለክለቡ አዳዲስ የሆኑ አካሄዶች እንደሚኖሩ ሁሉ ከአምና ይዟቸው የሚቀጥላቸው ነገሮችም እንደሚኖሩ የሚጠቁመው የአሰልጣኙ የመጨረሻ አስተያየት ” ቡናን አንድ እርምጃ ወደፊት ማሻገር ይኖርብናል። ክለባችን ዋንጫ ማሸነፍ አለበት። እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ለወጣቶች ዕድል መስጠታችንን እንቀጥላለን። ወጣቶቹ የቡና የወደፊት ተስፋዎች ናቸው። ችሎታቸውን አውጥተው እንዲያድጉ መርዳትም አለብን። ዘንድሮ ያደጉትም ተጨዋቾች እንደ አቡበከር ፣ ሚኪ እና ኃይሌ ብዙ ነገር የመስራት አቅም አላቸው። ከአመራሮቻችን ጋር በመሆንም አዳዲስ ነገሮችን ለማምጣት እየሞከርን ነው ፤ በልምምድ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የቡድኑ አወቃቀር ላይ። ለምሳሌ፡- በሜዳችን ስንሸነፍ ወይም ነጥብ ስንጋራ ጨዋታው እንዳለቀ ወደ የቤታችን ሳንበተን ወዲያውኑ በአንድነት ሆነን ወደ ካምፕ እንድናመራ አስቢያለው። በአውሮፓ ብዙዎች የሚጠቀሙበት መንገድ ነው ፤ የቡድኑን የማሸነፍ መንፈስም ለመጨመር እና በስህተቶቻችን ላይ ለመስራት ይረዳናል። ” የሚል ነበር።
ኢትዮጵያ ቡና በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ ሲገኝ ነገ በግማሽ ፍጻሜ ጅማ ኣባ ጅፋርን ይገጥማል ጥቅምት 17 በአዲስ አበባ ስታድየም ድሬዳዋ ከተማን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ደግሞ የውድድር ዓመቱን የሊግ ጨዋታዎች ይጀምራል።