የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የእግርኳሱ ዓለም የደረሰበት የአወቃቀር ደረጃ እንዲኖረው እና ለበርካታ አስርት ዓመታት ከሚመራበት ልማዳዊ አሰራር እንዲወጣ በማሰብ ባለፈው ዓመት የጥናት ቡድን በማዋቀር የሪፎርም ስራ ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ፌዴሬሽኑ ሊያሻሽላቸው ካሰባቸው መስኮች አንዱ የሆነው ደግሞ ከዚህ ቀደም ለእግርኳሱ የቀረበ እውቀት እና ልምድ በሌላቸው ኃላፊዎች በብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ ላይ በዘልማድ ይደረጉ የነበሩ አሰራሮችን (ለምሳሌ – የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች የቡድን መሪ በመሆን አልያም በሌሎች የብሔራዊ ቡድን ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት የሚፈጠሩት የአሰራር ክፍተቶች) ይቀይራል ብሎ በማመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ብቻ የሚመለከት ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተነግሯል። ቡድኑ በሁሉም የእድሜ ዕርከን የሚገኙ የወንድ እና የሴት ቡድኖችን ጉዳዮች የመከታተል እና የማስፈፀም ተግባር የሚኖረው ሲሆን በውስጡ የተለያዩ የስራ ዘርፎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል። የፊታችን ሐሙስ መደበኛ ስብሰባውን የሚያደርገው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ፌዴሬሽኑ ከዚህ ማሻሻያ ባሻገር በርከት ያሉ አስተዳደርን የተመለከቱ አዳዲስ አደረጃጀቶችን ይቀርፃል ተብሎ ሲጠበቅ በኮሚቴነት ከመጠቀስ አልፎ ለዓመታት ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የማይታየው የቴክኒክ ኮሚቴ በአዲስ መልክ ይዋቅራል ተብሎ ይገመታል።