የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | አዳማ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦችን የቅድመ ውድድር ዝግጅት አስመልክተን በምናቀርብላችሁ ፅሁፍ አሁን ደግሞ የአዳማ ከተማን ዝግጅት እናስዳስሳችኋለን።

ለ13 ዓመታት ከቆየበት ሊግ በ2005 ወርዶ ዳግም በ2007 የተመለሰው አዳማ ከተማ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከበላዩ ሁለት ክለቦችን አስቀድሞ በሦስተኝነት መጨረሱ የዋንጫ ተፎካካሪ የሚያሰኘው ነው። በሌላ መልኩ ከዚህ በላይ ውጤት አለማስመዝገቡ ደግሞ ሁሌም በድክመት ይነሳል። ይህን ታሪክ ለመቀየር ትክክለኛ ጊዜ ይመስል የነበረው የ2010 የውድድር ዓመት ደግሞ ክለቡ በለመደው ደረጃ ላይ እንዲቀመጥም ዕድል የሰጠው አልነበረም። ክለቡ በተለይም በጉዳት ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ተጨዋቾቹ ቁጥር በቀነሰበት ሁለተኛው ዙር ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ መስመሩ ምርጥ ስብስብ ካሏቸው የሊጉ ክለቦች በቀዳሚነት የሚሰለፍ ነበር። ሆኖም ብልጭ ድርግም በሚል አቋም እስከ 27ኛው ሳምንት በፉክክሩ ውስጥ ቆይቶ የነበረው አዳማ በመጨረሻ እጅ ሰጥቶ በ5ኛነት ዓመቱን አገባዷል። እኩል 11 ጨዋታዎችን በድል እና በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ክለቡ በቀሪዎቹ 8 ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ በ44 ነጥቦች ነበር ዓመቱን የጨረሰው። 26 ግቦችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ አሳርፎ በአንፃሩ ደግሞ 32 ግቦች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ ይዞ የነበረውን ስብስብ በማይመጥን ወጣ ገባ አቋም ዓመቱን በመዝለቁ ተደጋጋሚ ወቀሳን ሲያስተናግዱ የቆዩት አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ እና ምክትሎቻቸው ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል። በምትካቸውም በሼር ኢትዮጵያ እና አክሱም ከተማ የሚታወቀው አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም ለአዲሱ የውድድር ዓመት ቡድኑን ተረክቧል። በምክትል አሰልጣኝነት ተሹሞ በነበረው አሰልጣኝ ዳዊት ታደሰ በፍቃዱ ከኃላፊነት ከተነሳ በኋላ ደግሞ አሰልጣኝ ደጉ ዱባለን ቀጥረዋል።  ነገር ግን ዋና አሰልጣኙ በሊጉ ልምድ የሌላቸው መሆኑ ክለቡ የሚፈልገውን ከሦስተኝነት ከፍ ያለ ውጤት ለማምጣት ከሌሎች ክለቦች ጋር የሚኖረው ፉክክር እንዳይከብዳቸው የሚያሰጋ ነው። አሰልጣኝ ሲሳይ ግን በዚህ ሀሳብ አይሳማሙም። ” ከ2000 ጀምሮ እኔ ከአዳማ ጋር ነኝ። ከዛም ቀደም ብዬ ተጫዋች ነበርኩኝ። በአዳማ የሲ እና የቢ ቡድንን አሰልጥኛለው። በ2003 የዋናው ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆኜ ቡድኑ ላይ የመኪና አደጋ ሲደርስም ነበርኩኝ። በ2004 ደግሞ በ18 ጨዋታዋች ዋና አሰልጣኝ ነበኩ። ከዛም በከፍተኛ ሊግ በማሰልጠን ቆይቻለሁ። ይህም ሆኖ ግን ከአዳማ አላራቀኝም። አዳማን በቅርበት ነበር የምከታተለው ፤ ሊጉንም በደንብ አየው ነበር። በአጠቃላይ የኔና እና የአዳማ ነገር የቤተስብ ያህል ነው ፤ በጣም በቅርብ ነው የማውቀው። በሊጉ ምንም አዲስ ነገር እንደማይገጥመኝ እርግጠኛ ነኝ።” በማለት ኃላፊነቱ እንደማይከብዳቸው ተናግረዋል።

አዲስ ፈራሚዎች፡ ከግራ ወደ ቀኝ – ሱራፌል ዳንኤል፣ ብዙዓየሁ እንደሻው፣ ሐብታሙ ሸዋለም፣ አዲስዓለም ደሳለኝ፣ ሱራፌል ጌታቸው፣ ዐመለ ሚልኪያስ፣ ቴዎድሮስ በቀለ፣ ኄኖክ ካሳሁን፣ ዱላ ሙላቱ፣ ሙሉቀን ታሪኩ

አዳማ ከአሰልጣኝ ለውጡ ባለፈ አምና በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ በተደጋጋሚ ይጠቀምባቸው ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ፣ የመሀል ተከላካዩ ሙጂብ ቃሲም እና የመስመር አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸውን የሸኘው አዳማ  ከሦስቱ በተጨማሪም ተስፋዬ ነጋሽ ፣ ሲሳይ ቶሊ ፣ ሚካኤል ጆርጅ ፣ ደሳለኝ ደባሽ ፣ ወንደሰን ቦጋለ ፣ ፍርድዓወቅ ሲሳይ ፣ እንዲሁም በውሰት መጥቶ የነበረው ጫላ ተሺታንም አሰናብቷል። ዐመለ ሚልኪያስ (አማካይ ከመቐለ ከተማ) ፣ ቴዎድሮስ በቀለ (ተከላካይ ከመከላካያ) ፣ ሱራፌል ዳንኤን (መስመር አማካይ ከድሬዳዋ ከተማ) ፣ ሐብታሙ ሸዋለም (አማካይ ከወልድያ) እና ሮበርት ኦዶንካራ (ግብ ጠባቂ ቅዱስ ጊዮርጊስ) ክለቡ በለቀቃቸው ተጫዋቾች ምትክ ከሌሎች የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የመጡ ናቸው።  ከከፍተኛ ሊግ የመጡት ቀሪ ሰባት ተጫዋቾች ደግሞ ሙሉቀን ታሪኩ (አጥቂ ከባህር ዳር) ፣ ኄኖክ ካሳሁን (አማካይ ከሰበታ ከተማ) ፣ ዱላ ሙላቱ (መስመር አማካይ ከደቡብ ፖሊስ) ፣ አዲስዓለም ደሳለኝ (አማካይ ከሰበታ ከተማ) ፣ ሱራፌል ጌታቸው (አማካይ ከጅማ አባ ቡና) እና ብዙዓየሁ እንዳሻው (አጥቂ ከጅማ አባ ቡና) ናቸው። ከዚህ ውጪ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ሁለት ተጫዋቾች ያሳደገ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች ሦስት ተጫዋቹች ወደ ቡድኑ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።

በ2010 ለቻምፒዮንነት ከታጩ ቡድኖች መካከል በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ ሦስት ተጫዋቾችን ብቻ ማጣቱ አዳማን ዕድለኛ ያደርገዋል። የቀሪዎቹ ተጫዋቾች አቋም ከአንድ ዓመት በኋላ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ አዲሱ አሰልጣኝ በብዙው የተለወጠ ቡድን ያልገጠማቸው መሆኑ በራሱ መልካም ነገር ነው። ክለቡ ሦስቱን ቦታዎች ልምድ ባላቸው ተጨዋቾች እንደሚሸፈን የተጠበቀ ቢሆንም ተጠባባቂ ወንበሩን በጥቂቱ በአዳዲስ ፈራሚዎች በብዛት ደግሞ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ በሚያድጉ ተጫዋቾች ይተካል ተብሎ ተስቦ ነበር፡፡ ሆኖም እንደ ብዙሀኑ የሊጉ ክለቦች አዳማም ወደ ዝውውሮች ማድላቱ አልቀረም። አጠቃላይ የዝውውር እንቅስቃሴው ሲታይ ግን በተለይም በግብ ጠባቂ እና በመሃል ተከላካይ ቦታ ላይ ጥሩ ተጨዋቾችን ማግኘቱ አይካድም። አሰልጣኙም ስለእስካሁኖቹ ዝውውሮች ያላቸው አስተያየትም ” ዝውውሩ በጣም ጥሩ ነበር። አንደኛ ክለቡ በፋይናስ በኩል ተጠቃሚ ነው። ከዛ በተጨማሪ ወደ ክለቡ የመጡት ተጫዋቾች ራሳቸውን ለትልቅ ነገር ለማብቃት ያላቸው ስነ ልቡናዊም ሆነ ቴክኒካዊ ዝግጁነት  በጣም ጥሩ ነው። በእርገጠኝነት አዳዲሶቹ ፈራሚዎች አዳማ ከተማን የሚጠቅሙ ናቸው። ተጫዋቾቹ አዲስ እና ወጣት ቢሆኑም በቡድኑ ውስጥ ከ15 በላይ ሲኒየር ተጨዋቾችም አሉ። ይህም አዲሶቹ የተሻለ ልምምድ መቀሰም እንዲችሉ ያደርጋል።” የሚል ነው።

አዳማ ከተማ ዘግየት ብሎ አዲሱ ዓመት ከገባ በኋላ ነበር የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅቱን ማድረግ የጀመረው። ሆኖም የሚጠቀምበት የአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በክረምቱ የአንደኛ ሊግ ማጠቃለያ እንዲሁም የሀገር ዓቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ምዘና ውድድሮችን በማስተናገዱ ጥገና ስላስፈለገው ክለቡ ወደ ዝዋይ እንዲያመራ ሆኗል። መስከረም 3 ላይ ወደ ስፍራው በማቅናትም ተጫዋቾች ተጠቃለው ከገቡ በኋላ ከመስከረም 7 ጀምሮ ዝግጅቱን ማድረግ ጀምሯል። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ሲጀምሩም በውድድሩ ለመሳተፍ ወደ መዲናዋ የመጣው አዳማ ሱሉልታ ላይ ልምምዱን ቀጥሏል። አሰልጣኝ ሲሳይ የቡድኑን አጠቃላይ የዝግጅት ጊዜ አስመልክተው ሲያብራሩ ” ዝግጅት ስንጀምር መጀመሪያ ያደረግነው ተጫዋቾቹ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ መፈተሽ ነበር። በመቀጠል ባሳለፍነው ዓመት የነበረባቸውን ክፍተት እንዴት መሙላት እንዳለብን በተደጋገመ መንገድ በቀን ሁለቴ ለተወሰነ ቀናት በመስራት እና የተለያዩ ሙከራዋችን ያደረግን ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ  ውድድር በኋላ በአዳማ የሚቀሩንን ሙከራዋች እና ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወንን እንገኛለን። ” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዋንጫ ተሳትፎው ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አሳክቶ ከምድቡ የተሰናበተው አዳማ ከተማ በውድድሮቹ ላይ የታየበትን ክፍተቶች በቶሎ ማስተካከል ይጠበቅበታል። በተለይም በሦስቱ ጨዋታዎች ስድስት ግቦች የተቆጠሩበት መሆኑ እና ግቦቹ የተቆጠሩባቸው መንገዶች የቀድሞውን የመከላከል ጥንካሬውን መልሶ ለማግኘት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ያመላከቱ ነበሩ። አምናም ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚመጡ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ የሚታይበት የማስከፈት ችግሩ ዘንድሮም አብረውት እንዳይዘልቁ ያሰጋል።

አዳማ ከተማ በመጀመሪያ ሳምንት የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መክፈቻ ሜዳው ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል።