በካስቴል ቢራ የስያሜ ስፖንሰርነት በየዓመቱ በፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል የሚከናወነው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ለ7ኛ ጊዜ ዘንድሮ በተቀዛቀዘ ሁኔታ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ጅማሮውን ጥቅምት 4 አድርጎ እስከ ጥቅምት 10 የሚቆየው ይህ ውድድር ዛሬ በሁለተኛ ጨዋታ ሲዳማ ቡናን ከደቡብ ፖሊስ አገናኝቶ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይልቅ የእርስ በእርስ ሽኩቻወች እና ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወትን የተመለከትንበት ሲሆን ደቡብ ፖሊስ በእንቅስቃሴ ሲዳማ ቡና ደግሞ በሙከራዎች ተሸለው ታይተዋል፡፡ በ2ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ ዮናታን ፍሰሀ ከርቀት አክርሮ የመታት እና አዲሱ የደቡብ ፖሊስ ግብ ጠባቂ ዳዊት አሰፋ የመለሰበት በሲዳማ በኩል ሲጠቀስ በ15ኛው ደቂቃ ብሩክ በግል ብቃቱ ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ ከሳጥኑ ጠርዝ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ያወጣበት ሙከራ በደቡብ ፖሊስ በኩል መልካም የሚባለው የመጀመርያ አጋማሽ አጋጣሚ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ደቡብ ፖሊስ ተሻሽሎ ሲገባ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በዳዊት ተፈራ ያለቀላቸው አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም የግብ በሩን ሊከፍት የሚችል ተጫዋች ግን ሳንመለከት ቀርተናል፡፡ 69ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ባልቻ፣ 75ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ ከርቀት መትተው በተመሳሳይ ቋሚ ገጭቶ ሲወጣባቸው ሲዳማዎች በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ጫናቸውን በመጨመር ሐብታሙ ገዛኸኝ ላስቆጠር ያቃረበውን መልካም አጋጣሚ ተቀይሮ የገባው የፖሊስ ግብ ጠባቂ ሐብቴ ከድር መልሶበት ጨዋታው ያለምንም ግብ ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው የእለቱ ዋና ዳኛ ተከተል በተደጋጋሚ በሚሰጧቸው ውሳኔዎች በስታዲየሙ የነበረው ተመልካች ከፍተኛ ቅሬታን እንዲያሰማ ያደረገ ሲሆን በመሀል ለሚፈጠሩ የጨዋነት መጎደል መንስዔ ሲሆንም ታይቷል፡፡ ለዚህ ማሳያ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቅሬታን ባስከተለ ሁኔታ የፍፁም ቅጣት ምት መከልከላቸው እና አደገኛ አጨዋወትን መፍቀዳቸው ይጠቀሳል፡፡
ውድድሩ በመጪው ሐሙስ ሲጠናቀቅ ሦስት ነጥቦች ባለው ሀዋሳ ከተማ እና አንድ ነጥብ ባለው ሲዳማ ቡና መካከል በሚደረገው ጨዋታ የውድድሩ አሸናፊ የሚለይ ይሆናል፡፡