” የመጫወት አቅሙ አለኝ፤ ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ መራቄ ተፅዕኖ አያደርግብኝም ” ያሬድ ዝናቡ

ያሬድ ዝናቡ እግር ኳስን በሞጆ ከተማ ከጀመረ በኋላ በአዳማ ከተማ ለ6 ዓመታት የተሳካ ቆይታን አድርጎ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማምራት ለአራት ዓመታት በዋንጫ የታጀበ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል። በ1997 ከታዳጊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጀምሮ በ2004 ከ31 ዓመት በኋላ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካቶም ለታሪካዊው ጊዜ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን የድርሻውን ተወጥቷል። ከዚህ ውጪ በዋናው ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ማጣሪያዎች ላይ መጫወት ችሏል። ያሬድ ዝናቡ ወደ ደደቢት ካመራ በኋላ በጉዳት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ መጫወት ሳይችል ቀርቶ ከክለቡ ከተለያየ በኋላ ፋሲል ከነማን ቢቀላቀልም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ያልተሳካ ጊዜን አሳልፎ ከጎንደሩ ክለብ ጋር ሊለያይ ችሏል። አማካዩ ያሬድ ዝናቡ ከአንድ ዓመት በላይ ከሜዳ መራቁን ተከትሎ በብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ የት ነው ያለው የሚል ጥያቄን አስነስቷል። 

ይህን ሀሳብ መነሻ በማድረግም ተጫዋቹ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ስንል ጥያቄዎችን ይዘን ከያሬድ ዝናቡ ጋር አጭር ቆይታ ባደረግነው አጭር ቆይታ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከእግርኳስ ስላራቀው ጉዳት ተናግሯል። ” ከደደቢት ጀምሮ ከባድ የሆነ የተረከዝ ጉዳት ነበረብኝ። በሚቻለው መጠን ለመዳን ከፍተኛ የሆነ ምርመራ ባደርግም በፍጥነት መዳን ባለመቻሌ እንደሚታወቀው በ2009 የተወሰኑ የፋሲል ጨዋታዎች ላይ ከተሳተፍኩ በኋላ ከሜዳ ርቄያለሁ። በዚህ ምክንያት ነበር ከዕይታ የጠፋሁት።” ብሏል። 


በአዳማ በተከላካይ መስመር የሚታወቀውና በቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አማካይ ተጫዋችነት የተለወጠው ያሬድ ጉዳቱ ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ቢያርቀውም መጫወትን ስለማቆም እንደማያስብና እንደውም የመጫወት አቅም እንዳለወ ይናገራል። ” አላቆምኩም፤ እጫወታለሁ። ቅድም እንደነገርኩህ ለረጅም ጊዜ ያመኝ ስለነበረ በቂ የህክምና ክትትል አድርጌ እስክመለስ አቆይቶኛል። አሁን በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የምገኘው። ስለዚህም ዳግመኛ ወደ እግርኳሱ እመለሳለው እንጂ አላቆምም። አሁን በግሌ ልምዶችን እየሰራው እገኛለው። ለጊዜው አሁን ክለብ ባይኖረኝም የመጫወት አቅሙ ስላለኝ ክለብ ካገኘሁ እጫወታለሁ። ያለፉትን ዓመታት ከሜዳ መራቄ ምንም ተፅዕኖ አያደርግብኝም። አሁን ከጉዳቴ በሚገባ ስላገገምኩኝ በቅርቡ ወደ ሜዳ እመለሳለው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ” ሲል አስተያየቱን አጠቃሏል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ በቅርብ ጊዜያት ረጅም ጊዜያትን በጉዳት ካሳለፉ በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ይስተዋላል። አምና ለሁለት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በጉዳት ከሜዳ ርቆ የነበረው ነጂብ ሳኒ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ማምራቱም የሚታወስ ነው።