በጅማ አባ ጅፋር በ2010 የውድድር ዘመን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ትልቁን ሚና ከመወጣቱ ባሻገር በግሉ 23 ጎሎች በማስቆጠር በከፍተኘመ ጎል አስቆጣሪነት ያጠናቀቀው የኮከብ ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብፁ ክለብ ኢስማይሊ ቢያመራም ዝውውሩ የሰነድ ማጭበርበር ተፈፅሞበታል በማለት ፊፋ ዝውውሩን ሲያግድ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በበኩሉ በራሱ ህግ መሰረት ተጫዋቹ ፈፅሞታል ባለው ግድፈት መነሻነት የ6 ወር እና የ25 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አስተላልፎበት እንደነበረ ይታወቃል ።
የዚህ የቅጣት ውሳኔ ፊፋ እንዲያውቀው ከተደረገ በኋላ ባሳለፍነው ወር ለግብፁ ክለቡ ኢስማይሊ የመጀመርያ ጨዋታውን ማድረጉ በጊዜው በብዙ ስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ መነጋገሪ እንደነበረ ይታወሳል። ሆኖም ኦኪኪ ከዚህ ጨዋታ በኋላ በየትኛውም የግብፅ ሊግ ውድድሮች ላይ ለአዲሱ ክለቡ እየተጫወተ አይገኝም። የዚህ ምክንያት ምን እንደሆነ እና በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ስለ መባሉ አስመልክቶ በኢትዮጵያ የኦኪኪ አፎላቢ ህጋዊ ወኪል የሆነው አቶ ኤዶምያስ አስተያየቱን ሰጥቷል። ” ኦኪኪ በግብፅ እያሳለፈ ባለው የእግርኳስ ህይወቱ ደስተኛ አይደለም፤ ብዙ ጨዋታዎች ላይ እየተሳፈም አይገኝም። ከዚህ በተጨማሪ ሲሄድ በውል ደረጃ የተስማማው ደሞዙ እየተከፈለው እንዳልሆነ እና ቃል የተገባለት ጥቅማጥቅሞቹ እየተፈፀመለት አይደለም። በዚህ ምክንያት ከክለቡ ጋር ለመለያየት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ነገ ሐሙስ የክለቡ አመራሮች አንድ ነገር ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ” ሲል ገልፆልናል ።
የነገው ውሳኔ ኢስማይሊ ጋር መለያየት ከሆነ አኪኪ አፎላቢ በተሻለ የገንዘብ ፊርማ ወደ ኢትዮዽያ ዳግመኛ ተመልሶ የመጫወት ዕድል ሲኖረው ጅማ አባ ጅፋር የመጀመርያው ማረፊያው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል። ወደ ኢትዮዽያ ከመጣ በኋላ በፌዴሬሽኑ የተጣለበት የ6 ወር የቅጣት ውሳኔ ይነሳለታል ወይስ ቅጣቱን ጨርሶ ይጫወታል? የሚለውም በቀጣይ የሚታወቅ ይሆናል።