የከፍተኛ ሊጉ ክለብ አክሱም ከተማ በአዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን ማጠናከሩን በመቀጠል ስምንት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። ስድስቱ በፊርማ የመጡ ሲሆን ሁለት ተጫዋቾች ደግሞ ከተስፋ ቡድን ያደጉ ናቸው።
በድሉ መርዕድ (አማካይ ከጅማ አባ ቡና)፣ ፋሲል ገብረሚካኤል (አማካይ ከኢትዮጵያ ቡና)፣ ቴዎድሮስ መንገሻ (አጥቂ ከሀዲያ ሆሳዕና)፣ ትዕዛዙ ፍቃዱ (አጥቂ ከካፋ ቡና)፣ አብዮት ወንድይፍራው (ተከላካይ ከደቡብ ፖሊስ)፣ ዮሴፍ ኃይለማርያም (አማካይ፣ ከመቐለ ከተማ) ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው። ክብሮም ተኽላይ እና ዳዊት ታደሰ ደግሞ ከተስፋ ቡድን ያደጉ መሆናቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።
ከላይ የተገለፁትን ጨምሮ 10 ተጫዋቾችን ያስፈረመው አክሱም የስድስት ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል። ሰላማዊ ገብረስላሴ፣ ቴዎድሮስ መብራህቱ፣ ነጋሲ ኃይለ፣ ስለሺ ዘሪሁን፣ ልዑልሰገድ አስፋው እና ቢንያም ጌታቸው ውል ያደሱ ተጫዋቾች ናቸው።
በጌታቸው ዳዊት አሰልጣኝነት እየተመራ የሚገኘው አክሱም ከተማ በትግራይ ዋንጫ ላይ ሲሳተፍ የቆየ ሲሆን የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከመስከረም 18 ጀምሮ በአክሱም እያከናወነ ይገኛል።