በ13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተደርገው ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ወደ ፍፃሜው ማምራታቸውን አረጋግጠዋል።
በከባድ ዝናብ ታጅቦ በጀመረው የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ መከላከያን 3- 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ካስተናገደው ጨዋታ ባለፈ ውሃ የቋጠረው የአዲስ አበባ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳም የተጫዋቾችን ግምት እያዛባ ለተመልካቹ ተጨማሪ ተዝናኖትን ፈጥሯል።
ባህርዳር ከተማዎች ከጅማ አባ ጅፋር ያለግብ ከተለያዩበት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ተከላካይ ክፍላቸው ላይ ቴዎድሮስ ሙላቱ እና አሌክስ አሙዙን በሣለዓምላክ ተገኝ እና አስናቀ ሞገስ የተኩባቸውን ቅያሪዎች ሲያደርጉ መከላከያዎች ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 የረቱበትን ስብስብ ተጠቅመዋል።
በጨዋታው ብልጫን ወስደው ተደጋጋሚ ጫና ሲያሳድሩ እና በርካታ የማጥቃት ቅፅበቶችን ሲፈጥሩ የቆዩት ባህርዳር ከተማዎች የተከላካይ አማካዩ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት መትቶ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ ሆነዋል። ኳሷ ብዙ ኃይል ያላት ባትመስልም በቀላሉ ሊይዛት ተዘጋጅቶ የነበረው ይድነቃቸው ኪዳኔንን አልፋ ወደ ግብነት የተቀየረች ነበረች። ለግቧ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተንቀሳቀሱት መከላከያዎች ሁለት ከባድ ሙከራዎችን አድርገዋል። በዚህም 32ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ዓለሙ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ የመታው ኳስ አግዳሚውን ታኮ ሲወጣ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሌላኛው አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ ተመሳሳይ አደገኛ ሙከራ አድርጎ ምንተስኖት አድኖበታል።
ባህር ዳር ከተማዎች ሁለተኛውንም አጋማሽ በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ባደረገው የመስመር አጥቂ ግርማ ዲሳሳ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አክለው ነበር የጀመሩት። ግርማ በግራ መስመር ገብቶ ወደ ጎል የላካት ኳስ መረብ ላይ አርፋለች። በጊዜው ይድነቃቸው ኳሱ የሚሻማ እንደሚሆን በመገመት ተዘናግቶ ነበር። 48ኛው ደቂቃ ላይ ግን በሌላኛው የሜዳው ጥግ አዲሱ ተስፋዬ ከማዕዘን የተነሳን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች መከላከያዎች እንደ ፍፁም ገብረማርያም እና አቅሌሲያስ ግርማ ያሉ አጥቂዎችልቸውን በማስገባት እና በባህር ዳር ሜዳ ላይ አመዝነው በመጫወት በርካታ ሙከራዎችን አድርገዋል። ዳዊት ማሞ 65ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶት በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት ሙከራ ደግሞ ለግብ የቀረቡበት ዋነኛው አጋጣሚ ነበር።
ነገር ግን ቀጣይዋም ግብ የተቆጠረችው በጦሩ መረብ ላይ ነበር። 85ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አህመድ ዋቴራ በቀኝ መስመር በኩል ይዞ የገባውን የመልሶ ማጥቃት ኳስ ሲያሻግርለት ነፃ የነበረው ሌላው ተቀያሪ ማራኪ ወርቁ ተረጋግቶ በቀድሞው ክለቡ ላይ ሦስተኛዋን ግብ አስቆጥሯል። ውጤቱም ወደ 3-1 በመስፋቱ በጭማሪ ደቂቃ አቅሌሲያስ ግርማ ከምንይሉ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ማስቆጠሩ ልዩነቱን ከማጥበብ የዘለለ ትርጉም ለጦሩ ልትሰጥ አልቻለችም። በውጤቱ ባህርዳር ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለፍፃሜ መድረሱን አረጋግጧል። ከመስመር እየተነሳ በጨዋታው ብዙ ልዩነት ሲፈጥር የቆየው የክለቡ የመስመር አጥቂ ግርማ ዲሳሳ ደግሞ የጨዋታ ኮከብ በመሆን ተመርጧል።
በቀጣዩ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በቶማስ ስምረቱ እና አቡበከር ነስሩ የግንባር ጎሎች ጅማ አባ ጅፋርን በማሸነፍ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፍፃሜ ባህር ዳርን እንደሚፋለም አረጋግጧል።
በዚሁ ሁለተኛ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከጉዳት ያገገመው አቡበከር ነስሩን እና ከብሔራዊ ቡድን የተመለሱለት ተመስገን ካስትሮ ፣ አህመድ ረሺድ እና አማኑኤል ዮሀንስን በቀጥታ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ በማስገባት ከመከላከያው ጨዋታ አራት ለውጦችን አድርጓል። ጅማ አባ ጅፋርም ከባህርዳር ከተማ ጋር 0 0 ከተለያየበት ጨዋታ ተስፋዬ መላኩ ፣ ንጋቱ ገብረሥላሴን እና ዲዲዬ ለብሪን ወደ ተጠባባቂነት አውርዶ በምትካቸው ኤልያስ አታሮ ፣ ኄኖክ ገምቴሳን እና ኤርሚያስ ኃይሉን ተጠቅሟል። ኤልያስ ማሞ እና አስቻለው ግርማም ጨዋታውን ጀምረው የቀድሞው ክለባቸውን ገጥመዋል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ለቀድሞው አምበላቸው መስዑድ መሀመድ ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን ተጫዋቹም ስጦታውን ተቀብሎ ከቡና ሙሉ ስብስብ እና አሰልጣኖች ጋር ፎቶዎችን ተነስቷል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን ያሸነፉላቸውን ሁለት ግቦች በፍጥነት ነበር ያገኙት። 8ኛው ደቂቃ ላይ ቶማስ ስምርቱ ከሳምሶን ጥላሁን ወደ ቀኝ ያደላ የመሀል ሜዳ ቅጣት ምት 15ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አቡበከር ነስሩ ሁለተኛው ቋሚ ጋር ሆኖ ሉኩዋ ሱለይማን ከቀኝ መስመር ካሻገረለት ኳስ በግንባር በመግጨት ኢትዮጵያ ቡናን የ2-0 መሪ አድርገውታል። የጅማ አባ ጅፋር አጀማመርም ግን በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ኤርሚያስ ኃይሉ 5ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውስጥ 9ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከሳጥን ውጪ ያደረጋቸውን ጠንካራ ሙከራዎች ግብ ከመሆን የታደጋቸው ዋቴንጋ ኢስማ ነበር።
ምናልባትም ዲዲዬ ጎሜስ በዚህ ዓመት ቡድናቸው እንዲኖረው የሚፈልጉትን ዓይነት እንቅስቃሴ በመጀመሪያው አጋማሽ የተመለከቱ ይመስላል። በቶሎ ኳስ ማስጣል እና ከባድ የቀኝ መስመር ጥቃት የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎኖችም ነበሩ። ድንቅ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፈው ዳንኤል ደምሴ ከአስራት ቱንጆ ተቀብሎ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም ሳምሶን እና አማኑኤል ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች ቡድኑ በነዚሁ ወቅቶች ወደ ግብ ከደረሰባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ ይካተታሉ።
ግብ እስኪያገኙ ተቀዛቅዘው የታዩት አባ ጅፋሮች 52ኛው ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አግኝተዋል። ኤልያስ ሞሞ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ግርማ ነበር ወደ ግብነት የለወጠው። ግብ ከማግኘታቸው ባለፈ እንደመጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮም ጅማዎች ከባባድ ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም። ኤርሚያስ 54ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ደግሞ 62ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርተው የመቷቸው ኳሶች ለጥቂት ነበር ወደ ውጪ የወጡት። አባጅፋሮች እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስም ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተጭነው ተጫውተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥም ተቀይሮ የገባው አይቮሪኮስታዊው አጥቂ ዲዲዬ ለብሪ አንዴ ከጎሉ አፋፍ ቀጥሎም ከመሀል ሜዳ ያደረጋቸው ሙከራዎች የዋቴንጋን የግብ ጠባቂነት አቅም የፈተሹ ነበሩ።
የመጀመሪያው የበላይነታቸው እየቀነሰ የመጣው ኢትዮጵያ ቡናዎች ጫናው በርትቶባቸው ቢዘልቁም እነሱም አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም። 55ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሌላ የግንባር ኳስ ሞክሮ የሳተበት እና አህመድ ረሺድ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሞክሮ ዳንኤል አጃዬ የመለሰበት ሙከራዎች በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን 88ኛው ደቂቃ ላይም ዳንኤል ተቀይሮ የገባው ሚኪያስ መኮንንን ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቶት ሚኪያስ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በስታድየሙ ፓውዛ መጥፉት 28 የዕረፍት ደቂቃዎችን ያሳለፈው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ቡናን ለፍፃሜው አሳልፎ ተጠናቋል። የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠው ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር ተከላካይ ተካልኝ ደጀኔ ነበር።