የግራ መስመር ተከላካይ የሆነውን አይቮሪኮስታዊው ያኦ ኦሊቨር ኩዋኩ በአንድ ዓመት ውል ወደ ሀዋሳ አምርቷል።
ሀዋሳ ከተማ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ ምንተስኖት አበራን እና አዳነ ግርማን ብቻ በማስፈረም ከሌሎች ጋር ሲነጻፀር ጥቂት ተሳትፎ ነበር ያደረገው። አሁን ደግሞ ክለቡ ሦስተኛውን ተጫዋች ወደ ቡድኑ የቀላቀለ ሲሆን አዲሱ ፈራሚ አይቮሪኮሰት ዜግነት ያለው የግራ መስመር ተከላካዩ ያኦ ኦሊቨር ኩዋኩ ነው። ኩዋኩ በአንድ ዓመት ውል ነው ወደ ደቡቡ ክለብ ያመራው።
የ32 ዓመቱ ተከላካይ በኮትዲቫር ሊግ ለኤ ኤስ ታንዳ ስፖርት ክለብ የተጫወተ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ለሙከራ ከመጣ ከአምስት ወራት በላይ አሳልፎ የመጨረሻ ማረፊያውን በሀይቆቹ ቤት አድርጓል። አብዛኛው የእግር ኳስ ህይወቱ በሀገሩ ክለቦች የተጫወተው ኩዋኩ ከኤ ኤስ ታንዳ በተጨማሪ ለጄ ኤስ ካቲዮላ እንዲሁም ያለፉትን ሦስት የውድድር ዓመታት ደግሞ ለዋና ከተማው የአቢጃን ክለብ አፍሪካ ስፖርትስ በመጫወት አሳልፏል። ከ19 ዓመት በታች የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን አባል የነበረው ተጫዋቹ ከክለቡ የቦታው ተቀናቃኞች ደስታ ዮሀንስ እና ዮሀንስ ሴጌቦ ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቀው ይገመታል።
በሌላ በኩል በአጥቂ ስፍራ ላይ ክፍተት ያለበት ክለቡ አስፈርሞት ከነበረው ቶጎዊው አጥቂ አጉዲ ፎቪ ጋር በጉዳት ምክንያት ከተለያየ በኃላ ሁለት የውጭ አጥቂዎችን በማምጣት የሙከራ ጊዜን ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም አመርቂ እንቅስቃሴን አላደረጉም በሚል እንዳሰናበታቸው ታውቋል። በምትካቸውም ከናይጄሪያ የፊት መስመር ተሰላፊ ለሙከራ ማምጣቱ ተሰምቷል፡፡