በተሻሻሉ ህጎች ላይ ለዳኞች ፤ ለኮሚሽነሮች እንዲሁም ለክለብ አመራሮች እና ለተጫዋቾች ስልጠና ሊሰጥ ነው።
የ2010 የውድድር ዓመት በርካታ የውዝግብ መነሻ የሆኑ ነገሮችን አሳይቶን ያለፈ ነበር። በተለይም ከዳኝነት ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ጉዳዮች የስፖርቱን ወቅታዊ ህግጋት ካለመረዳትም ጭምር እንደሚከሰቱ የብዙዎች ዕምነት ነው። ይህን ከግምት በማስገባትም ይመስላል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሜቴ በያዝነው ዓመት የተሻሻሉ የጨዋታ ህግጋትን ለተጫዋቾች እና ለክለብ አባላት በሙሉ በቂ ኢንስትራክተሮችን በመመደብ ለአንድ ቀን ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል። ኮሚቴው ያዘጋጀው ስልጠና በቅድሚያ ለፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይ እንደ ውድድሮች ዕርከን ስልጠናው እንደሚቀጥል ታውቋል። በዚህም መሰረት ሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለስልጠናው የሚመቻቸውን ቀን እንዲያሳውቁ በደብዳቤ ተጠይቀዋል።
ኮሚቴው የተሻሸሉትን ህጎች አስመልክቶ ለፕሪሚየር ሊግ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች በሚቀጥለው ሳምንት በተከታታይ ለሶስት ቀናት የሚዘጋጅ ስልጠና እንደሚሰጥም ጨምሮ አስታውቋል። የዳኞችን የስልጠና ወጪ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲሆን በከፍተኛ ሊግ እና በአንደኛ ሊግ ያሉትም ዳኞች ስልጠናውን በቀጣይ እንደሚወስዱ ተገልጿል።