ፋሲል ከነማ ዮሴፍ ዳሙዬን ከድሬዳዋ በሁለት ዓመት ኮንትራት ውል አስፈርሞታል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ የተስፋ ቡድኖች ተጫውቶ ያሳለፈው ዮሴፍ ዳውዬ በ2008 የውድድር ዓመት ወደ ሌላኛው የመዲናዋ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና አምርቷል። እስከ 2009 የውድድር ዓመት አጋማሽ ቆይቶም ቀጣይ ማረፊያውን በድሬዳዋ ከተማ ነበር ያደረገው። ያለፈውን አንድ ዓመት ከግማሽ በምስራቁ ክለብ ያሳለፈው የአጥቂ አማካዩ አሁን ደግሞ የአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜን በማሳለፍ ወደ የአፄዎቹን ቤት ተቀላቅሏል። እስከ 2012 መጨረሻም በጎንደሩ ክለብ እንደሚቆይ ይገመታል።
በዝውውር መስኮቱ ሰፊ ተሳትፎን እያደረጉ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች የዮሴፍ ዳሙዬን ዝውውር ጨምሮ አስራሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን በቡድናቸው ውስጥ አካተዋል። ቡድኑ በአማካይ ክፍሉ ላይ ከአዳዲሶቹ ሀብታሙ ተከስተ ፣ በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው ከነባሮቹ ደግሞ እንደ ኤፍሬም አለሙ እና ያስር ሙገርዋ ያሉ የመሀል ክፍል ተጫዋቾችን በመያዙ የዮሴፍ መምጣት ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጨማሪ አማራጭ የሚፈጥር ይገመታል።