ሲዳማ ቡና የደቡብ ካስቴል ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል

ሲዳማ ቡና የስፖንሰር ስያሜው መጠናቀቂያ ዓመት ላይ በሆነው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ቻምፒዮን መሆን ችሏል።

ካለፉት ዓመታት እጅግ በተቀዛቀዘ ሁኔታ በሦስት ክለቦች መካከል ብቻ ከጥቅምት 4-10 ሲደረግ የነበረው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ውድድር ፍፃሜ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል ተደርጎ ሲዳማ ቡና 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ 09፡00 ላይ በጀመረው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡና በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሀዋሳ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች የመጠናናት አይነት እና አሰልቺ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ቢሆንም ቀስ በቀስ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ቅኝት መግባት ችለዋል። በተለይን ለሲዳማ ቡና ተቀይሮ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው አዲሱ ፈራሚ ዳዊት ተፈራ የተሳኩ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ በመስጠት ልዩነት ፈጣሪነቱን አሳይቷል። በአንፃሩ መረጋጋት ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ኳስን በአግባቡ የመቆጣጠር ችግራቸው ብልጫ እንዲወሰድባቸው ምክንያት ሆኗል። 

10ኛ ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ የሰጠውን ኳስ በውሰት ወደ ወላይታ ድቻ አምርቶ የነበረው አጥቂው ፀጋዬ ባልቻ ሞክሮ ሶሆሆ ሜንሳ መልሶበታል። ይሁን እና 13ኛው ደቂቃ ላይ ከብሔራዊ ቡድን የተመለሰው አዲስ ግደይ የዳዊት ተፈራን ሌላ የተሳካ ኳስ ተጠቅሞ ስዳማን መሪ አድርጓል። ወደ ሀዋሳ የግብ አፋፍ በተደጋጋሚ መድረሳቸውን የቀጠሉት ሲዳማዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱ ኮከብ ዳዊት ባስጀመረው እና ሀብታሙ ተፈራ ባቀበለው ኳስ በአዲስ ግደይ አስቆጣሪነት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። 


በአዳነ ግርማ እና እስራኤል አሸቱ ሙከራዎችን ለማድረግ የጣሩት ሀይቆቹ ደግሞ የተሳኩ ቅብብሎችን መከወን ተስኗቸው ውጤቱን ማጥበብ ሳይችሉ ወደ ዕረፍት አምርተዋል። 
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ተሽለው ወደ ሜዳ የገቡት ሀዋሳዎች በቅያሪዎቻቸው ታግዘው ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደረጉ የሲዳማ ቡናዎች አቀራረብ  ደግሞ ፍፁም ተቀይሮ በሀዋሳ ብልጫ እንዲወሰድባቸው አድርጓል። ነገር ግን ሀዋሳዎችም የወሰዱትን ብልጫ ወደ መጨረሻ የግብ ዕድልነት በመቀየሩ በኩል ተቸግረው ታይተዋል። 66ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ድልቢ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታት ኳስ ግን መሳይ አያኖ መረብ ላይ አርፋ ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ዕድል ብትፈጥርም ውጤቱ ሳይቀየር ሲዳማ ቡናዎች ከእረፍት በፊት ባስቆጠሯቸው ግቦች ታግዘው 2-1 አሸንፈዋል። 


በጨዋታው ሂደት ከታዩ ሌሎች ጉዳዮች መካከል የዕለቱ ዋና ዳኛ ባህሩ ተካ ሐብታሙ ገዛኸኝ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ተሰርቶበት ለራሱ ቢጫ ያሳዩበት ውሳኔ አነጋጋሪ ነበር።
ሲዳማ ቡናዎች ለሰባተኛ ጊዜ በተዘጋጀው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ሻምፒዮን በመሆን ከአቶ ገልገሎ ገዛኸኝ የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እጅ የዋንጫ ሽልማታቸውን ወስደዋል።


በቀጣይ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች የካስቴል ዋንጫ ውድድር ከጥቅምት 18 ጀምሮ በዱራሜ ከተማ ከ10 በላይ ክለቦችን በማሳተፍ እንደሚጀምር ይጠበቃል። በተጨማሪም የክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በክልሉ የሚገኙ የሴቶች ቡድኖችን ጨምሮ ተጋባዥ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን ተሳታፊ የሚያደርግ የአቋም መፈተሻ ውድድር የደቡብ ካስቴል የሴቶች ውድድር በሚል መጠሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማከናወን መዘጋጀቱን አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ የፌድሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡