አንጋፋው አጥቂ አንዱዓለም ንጉሴ “አቤጋ” በአንድ ዓመት የውል ኮንትራት ለጦና ንቦቹ ፊርማውን አኑሯል፡፡
በሊጉ ለረጅም ዓመታትን በወጥ አቋማቸው ከዘለቁ ተጫዋቾች መካከል በግንባሩ በመግጨት በሚያስቆጥራቸው ጎሎች የሚታወቀው አንጋፋው የፊት መስመር ተሰላፊ አንዱዓለም ንገሴ አንዱ ነው። በ1994 በውጤታማነቱ ከሚጠቀሰው ሙገር ሲሚንቶ ወጣት ቡድን ከተገኘ በኃላ በዛው በሙገር ዋናው ቡድን ቆይታ አድርጎ በ1996 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምርቷል። በፈረሰኞቹ እስከ 2000 በነበረው የመጀመርያ ቆይታ ምርጥ ጊዜን በክለቡ ሲያሳልፍ በ2001 ወደ ሰበታ አቅንቶ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመመለስ ለሁለት ዓመታት መጫወት ችሏል። በ2004 ወደ ሀዋሳ ከተማ ከዚያም በ2006 ሲዳማ ቡና አምርቶ እስከ 2008 ቆይቷል። “አቤጋ” በመቀጠል ማረፊያውን ያደረገው ወልዲያ ሲሆን በግሉ ምርጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ወሳኝነቱን አስመስክሯል። አሁን ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ዳግም ተመልሶ ወላይታ ድቻን ከአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ በኋ መቀላቀል ችሏል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ከአዲሶቹ የክለቡ ፈራሚዎች ባዬ ገዛኸኝ እና ሳምሶን ቆልቻ እንዲሁም ከነባር የክለቡ ተጫዋቾች ጋር ለመጀመርያ ተሰላፊነት ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡