በሊጉ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ፅሁፋችን ለዛሬ የስያሜ ለውጥ ወዳደረገው መቐለ ሰብዓ እንደርታ ይወስዳችኋል።
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገሪቱ የመጀመሪያ ሊግ አድጎ እስከ መጨረሻው ሳምንታት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የቆየው መቐለ በመጨረሻም አራተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል። ዓመቱ ከመጀመሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ካሳደጉት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ጋር ተለያይቶ በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስር በመቀጠል የጨረሰበት የአራተኝነት ደረጃ በብዙዎች ያልተገመተ ነበር። ከጅማ አባ ጅፋር ቻምፒዮንነት ታሪክ ቀጥሎም ከታች እንደመጣ ክለብ ያስመዘገበው ውጤት በትልቅነቱ የሚጠቀስ ነው። የያኔው መቐለ ከተማ ሊጉን በ49 ነጥቦች ሲያጠናቅቅ 13 ጨዋታዎችን አሸንፎ ፤ አስሩን በአቻ ሰባቱን ደግሞ በሽንፈት ነበር የጨረሰው። ከወገብ በላይ ካጠናቀቁ ክለቦች መካከል ዝቅተኛውን 26 ግቦች በማስቆጠር እንዲሁም ከአባ ጅፋር ቀጥሎ በቁጥር ዝቅተኛ የሆኑ 15 ግቦችን ያስተናገደ ክለብ ሆኖ ውድድሩን አገባዷል።
ዓመቱ ተጠናቆ የክረምቱ ጊዜ ሲገባ እንደብዙዎቹ ክለቦች መቐለም በርካታ ለውጦችን አድርጓል። በቅርቡ ወደ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ያደረገው የስያሜ ለውጥ እንዳለ ሆኖ የአምናው ውድድር እንደተገባደደ ክለቡ ከዋና አሰልጣኙ ዮሃንስ ሣህሌ እና ከ15 ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል። በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ ምትክም ጅማ አባ ጅፋርን ለሊግ ክብር ያበቁት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌን ሾሟል። ቶክ ጀምስ ፣ እያሱ ተስፋዬ ፣ ካርሎስ ዳምጠው ፣ መድሀኔ ታደሰ ፣ ፍቃዱ ደነቀ ፣ ፉሰይኒ ኑሁ ፣ ጋይሳ ቢስማርክ ፣ ዐመለ ሚልኪያስ ፣ ሀብታሙ ተከስተ ፣ ዳንኤል አድሃኖም ፣ ዳዊት ዕቁበዝጊ ፣ ኃይሉ ገብረእየሱስ እንዲሁም በውሰት ውል ወደ ሌሎች ክለቦች አምርተው የነበሩት ክብሮም አስመላሽ ፣ ሙሴ ዮሀንስ እና ሐዱሽ አወጣኸኝ ከክለቡ የተለያዩት ተጫዋቾች ናቸው።
በሊጉ በመከላከል ጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ ቡድኖች አንዱ የነበረው መቐለ ምንም እንኳን ያስመዘገበው ውጤት መልካም ቢሆንም ቡድኑ የነበረው የጥልቀት ውስንነት እና የተጫዋቾች ጥራት ማነስ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ይበልጥ እንዳይገፋ እንዳደረገው ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ባለፈው ዓመት በሁለቱም የዝውውር መስኮቶች ያደረጋቸው ዝውውሮች የአብዛኞቹ ያልተሳካ መሆን አብሮ የሚነሳ ሌላኛው ምክንያት ነበር። የዘንድሮዎቹን ፈራሚዎች በተመለከተ ግን የቡድኑ አዲሱ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እንዲህ ሲሉ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ” ዝውውሮቹ በአመዛኙ (ወደ 75%) በጣም ጥሩ የሚባሉ እና የሚያስጨበጭቡ ናቸው። እንደ ሀይደር እና ጂብሪል ያሉት ተጫዋቾች እንደውም በፍጥነት በደጋፊው ሁሉ ትልቅ ተቀባይነትን አግኝተዋል። ነባሮቹ ተጫዋቾችም ከፍተኛ መሻሻልን አሳይተዋል።”
ከባለፈው ዓመት ቋሚ ተሰላፊዎቻቸው ጋር በአብዛኛው መለያየታቸው ተከትሎ በገበያው በሰፊው የተሳተፉት መቐለ ሰብዓ እንደርታዎች በዘንድሮው የዝውውር መስኮት አስራአንድ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል። ከአዲሶቹ ፈራሚዎች መካከል ጋብርኤል መሕመድ (ከሀዋሳ ከተማ) ፣ አሚኑ ነስሩ እና ዮናስ ገረመው (ከጅማ አባ ጅፋር) ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ (ከኢኮስኮ) ፣ ሀይደር ሸረፋ (ከጅማ አባ ቡና) ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ (ከመከላከያ) ፣ ኃይለአብ ሃይለስላሴ (በጉዳት ክለብ አልባ የነበረ) የአማካይ መስመር ተጫዋቾች ናቸው። ከወልዲያ የመጡት ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ያሬድ ሃሰን እንዲሁም የደደቢቱ ስዩም ተስፋዬ ደግሞ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ሲሆኑ ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከሀገረ እንግሊዝ የመጣው አርዓዶም ገብረህይወት እስካሁን በአጥቂ መስመር ላይ የፈረመ ብቸኛው ተጫዋች ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ ለጋናዊው አጥቂ ኦሰይ ማውሊ የሙከራ ዕድል ሰጥቶ የነበረው ክለቡ አሁን ደግሞ ቱንዴ ኢናሀሮ የተባለ ናይጄሪያዊ አጥቂን እየተመለከተ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት የመቐለ ሰብዓ እንደርታን የማጥቃት ክፍል ሲመሩ የነበሩት ጋይሳ ቢስማርክ ፣ መድሀኔ ታደሰ እና ፉሴኒ ኑሁ ከክለቡ መለያየታቸውን ተከትሎ በዚህ የዝውውር መስኮት የአጥቂ ክፍል ተሰላፊዎች ለማስፈረም በሰፊው ወደ ገበያ የወጣው ክለቡ እስካሁን ድረስ አርዓዶም ገብረህይወትን ብቻ ማስፈረሙን ተከትሎ በቀሩት ቀናቶች ሌላ የአጥቂ ክፍል ተሰላፊ ያስፈርማሉ ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጓል። በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በተናጠል ለቡድኑ ውጤት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ ፍሊፔ ኦቮኖ እና አምበሉ ሚካኤል ደስታ በዚህም ዓመት ከክለቡ ጋር መቀጠላቸው በበጎ የሚነሳ ነው።
መቐለዎች መቀመጫቸው በሆነው የመቐለ ከተማ ከነሀሴ 17 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ለሰባት ሳምንታት ሲያከናውኑ ቆይተዋል። መስከረም 26 በተጀመረው የትግራይ ዋንጫ ላይ ያደረጉት ተሳትፎም በአሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በአዲሱ ክለባቸው የገጠማቸው ከባቢ ለዝግጅቱ እንደተመቻቸው ከአስተያየታቸው መረዳት ይችላል። ” ከደጋፊው ጀምሮ በክለቡ አመራሮች ዙሪያ ያለው ፍላጎት እና እኔን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸው በመልካም ጎን የሚጠቀስ ነው። ይህም የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅቱ ሳይቆራረጥ የሜዳን ጨምሮ ምንም ችግር ሳይኖር በዕቅዴ መሰረት እንድሄድ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ” ይላሉ። አሰልጣኙ እንደሚናገሩት በሰባቱ ሳምንታት ዝግጅት ወቅት ዋነኛ ትኩረታቸው የነበረው ተጫዋቾቻቸውን ከእሳቸው የአጨዋወት አስተሳሰብ ጋር እንዲዋሀዱ ማድረግ ነበር። “ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ስትዘዋወር የምታገኘው የተለያዩ ተጫዋቾችን ነው። እነዛን ተጨዋቾች ወደ ራስ ፍልስፍና ማምጣት ደግሞ የግድ ነው። ያን ደግሞ ሁሉም ተጫዋቾች በእኩል ፍጥነት አይረዱትም። እነርሱን ለማስተካከል የተወሰነ ጥረት ይፈልግ ነበር። ሆኖም አሁን ላይ በደንብ ቅርፅ ያለው ቡድንን ማየት ይቻላል።” የሚለው አስተያየታቸውም ሀሳቡን የሚደግፍ ነው።
ክለቡ ባለፈው ዓመት ከነበሩት ጠንካራ ጎኖች ዋነኛው የመከላከል አደረጃጀቱ ነበር። ላስመዘገበው ውጤትም ጥቂት ግቦችን ማስተናገዱ በእጅጉ እንደረዳው መናገር ይቻላል። በአዲሱ የውድድር ዓመት ክለቡ የአማካይ ክፍሉ ላይ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ቁጥር እና የጨዋታ ባህሪያቸው ሲታይ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ አጨዋወቱን ቀይሮ ሊመጣ እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል። በአሸናፊነት ያጠናቀቀው የትግራይ ዋንጫ ላይም የታየው ይሄው ነበር። በውድድሩ ወደ ራሱ ግብ ክልል በእጅጉ ተጠግቶ የሚከላከል እና በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚው መድረስን የሚመርጠው መቐለ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ የመስጠት ዝንባሌን አሳይቷል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ክለቡ ጠንካራ ተፎካካሪ ከመሆን አልፎ ለዋንጫ እንደሚጫወት ገልፀው ቡድኑ በቀጣይ ዓመት የራሱ መለያ ያለው አጨዋወት እንደሚኖረው ተናግረዋል። አሰልጣኙ አክለውም ቡድኑ ወጥነት ያለው ስብስብ ይዞ እንደሚቀጥል እና የአከባቢው ታዳጊዎች በቡድኑ ውስጥ ዕድል የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ለመስራት በሰፊው እንዳቀዱ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪም አሰልጣኙ ቡድኑ አዲስ ስብስብ ይዞ ቢቀርብም በቀጣይ ዓመት ጠንካራ ሆኖ እንደሚቀጥል ያላቸውን ዕምነት ሲገልፁ “እንደ ቡድን የሚንቀሳቀስ ፣ ኳስን መስርቶ የሚጫወት ፣ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚያጠቃ እና ጎል የሚያስቆጥር ቡድን ነው ይዘን ምንቀርበው። በአጠቃላይ ቡድናችን በቀጣይ ዓመት አዝናኝ እግር ኳስን የሚጫወት እና የሚያጠቃ ቡድን ይሆናል።” ብለዋል።