​የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | ጅማ አባ ጅፋር

ከቀናት በኋላ ለሚጀመረው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በምን መልኩ ሲዘጋጁ እንደከረሙ የምንመለከትበት ፅሁፋችን ዛሬ ጅማ አባ ጅፋርን ያስቃኘናል።

የቀድሞው ጅማ ከተማ በሁለተኛው የሀገሪቱ የሊግ ዕርከን ቆይቶ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ እና ጅማ አባ ጅፋር ተብሎ የአምናውን የውድድር ዓመት ሲጀምር የሊጉን ዋንጫ ያነሳል ብሎ የገመተ አልነበረም። አስራ አምስት ተጫዋቾችን እንደ አዲስ አስፈርሞ በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ስር እስከ ስድስተኛው ሳምንት በአንድ ድል ብቻ የተጓዘው ክለብ ግን ዓመቱ ሲገባደድ የሊጉ ቻምፒዮን መሆን ችሏል። ቡድኑ 15 ጨዋታዎችን አሸንፎ 10 አቻ በመውጣት አምስት ጊዜ ደግሞ ተሸንፎ በ55 ነጥቦች ነው ሊጉን በበላይነት የጨረሰው። ጅማ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ የተቆጠረበት ክለብም ነበር (15) ፤ 39 ጊዜ ደግሞ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ይህንን ታሪካዊ ድል ተከትሎም አባ ጅፋር በ2019ኙ የቶታል የአፍሪካ ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል።

አስገራሚውን የውድድር ዓመት ካጠናቀቀ በኋላ የመጡት ለውጦችን ስንመለከት ጅማ አባ ጅፋር ልክ አምና በተጓዘበት መንገድ ላይ መሆኑን እነረዳለን። አሰልጣኝ ገብረመድኅንን ጨምሮ በብዛት የአንድ ዓመት ውል ብቻ የነበራቸው የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ክለቡን ለቀዋል። በተለይም በውድድር ዘመኑ አስገራሚ ጉዞ ውስጥ በተደጋጋሚ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በመካተት ትልቅ ሚና የነበራቸው ኄኖክ አዱኛ ፣ አሚኑ ነስሩ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ኄኖክ ኢሳያስ ፣ ተመስገን ገብረኪዳን እና ኦኪኪ አፎላቢን ጨምሮ ቢኒያም ሲራጅ ፣ ሳምሶን ቆልቻ ፣ እንዳለ ደባልቄ ፣ አሮን አሞሀ ፣ ዳዊት አሰፋ ፣ ብሩክ ተሾመ ፣ ኢብራሂም ከድር ፣ ነጂብ ሳኒ ፣ ቢኒያም ታከለ እና ፍራዎል መንግስቱ ከጅማው ክለብ ጋር ተለያይተዋል። ክለቡ በዝውውር ገበያው በሌሎች ክለቦች ፍጥነት ባለመሄዱም አህጉራዊ ውድድር ላይ ከመሳተፉ ጋር ተደምሮ በወቅቱ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎት ነበር። ሆኖም በሂደት ከአሰልጣኝ ቅጥር ጀምሮ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረሙ ነገሮች መልክ የያዙ መስለዋል። 


በአሰልጣኝ ቅጥር በኩል አምና ከወልዲያ ጋር የነበሩት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድኑን ተረክበዋል። አሰልጣኙ በቀድሞው ክለባቸው ሳሉ የአንድ ዓመት ቅጣት የተላለፈባቸው መሆኑ ይታወሳል ፤ የቅጣቱን ግማሽ በማጠናቀቃቸውም በቀጣይ ጉዳያቸው በይግባኝ እንደሚታይ ይጠበቃል። በመቀጠል ክለቡ 15 ተጫዋቾችን ከተለያዩ የሀገር ውስጥ ክለቦች እንዲሁም ከውጪ አስመጥቷል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ቡናዎቹ መስዑድ መሀመድ (አማካይ) ፣ ኤልያስ ማሞ (አማካይ) ፣ አክሊሉ ዋለልኝ  (አማካይ) እና አስቻለው ግርማ (የመስመር አጥቂ) ፤ የኢትዮ ኤሌክትሪኮቹ ዐወት ገብረሚካኤል (የመስመር ተከላካይ) ፣ ዲዲዬ ለብሪ (አይቮሪኮስታዊ የመስመር አጥቂ) እና ተስፋዬ መላኩ (ተከላካይ) እንዲሁም የፋሲል ከነማዎቹ ኤርሚያስ ኃይሉ ፣ ከድር ኸይረዲን (መሀል ተከላካይ) እና ኄኖክ ገምቴሳ (አማካይ) ወደ ምዕራቡ ክለብ የመጡ ሲሆን ዘሪሁን ታደለ (ግብ ጠባቂ) ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሚኪያስ ጌቱ (ግብ ጠባቂ) በድጋሜ የተቀላቀለ ፣ ብሩክ ገብረአብ (አጥቂ) ከሽረ እንደስላሴ ፣ ቢስማርክ አፒያ (ጋናዊ አጥቂ ከሞልደስት ሉቺኒ ሰረቢያ) እና ያሬድ ዘውድህ (ተከላካይ) ከድሬዳዋ ከተማ ጅማን የተቀላቀሉ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ተቀይሮ የመግባት ዕድል ያገኘው ሌላኛው አጥቂ ማማዱ ሲዲቤም ከሰሞኑ በይፋ የክለቡ ተጫዋች እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ .እንደ ክለቡ አሰልጣኝ ሀሳብ ከሆነም ቡድኑ የአዲስ አበባ ዋንጫ ፣ የአሸናፊዎች አሸናፊ እንዲሁም የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ ወደ ጅማ ሲመለስ ከዛው የተመለመሉ ወጣት ተጫዋቾችን እንደሚያካትት ይጠበቃል። ነባሮቹን ዳንኤል አጃዬን እና አዳማ ሲሶኮን ጨምሮ አዲስ ፈራሚዎቹ ዲዲዬ ለብሪ ፣ ቢስማርክ አፒያ እና ማማዱ ሲዲቤ በክለቡ ውስጥ የሚጫወቱ አምስት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ጅማ አባ ጅፋር በአምናው የውድድር ጊዜ ጥሩ የመከላካል ሪከርድ ነበረው። በጨዋታ በአማካይ 0.5 ግብ አስተናግዶ በጨረሰው ቡድን ውስጥ የነበሩት ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃዬ ተከላካዮቹ አዳማ ሲሴኮ እና ኤልያስ አታሮ መቆየታቸውም እንደመልካም የሚወሰድ ነው። ክለቡ አማካይ ክፍል ላይም በአንድ ክለብ ውስጥ በተለይም ከኢትዮጵያ ቡና አብረው የቆዩ ተጫዋቾችን ማምጣቱ የውህደት ስራውን ሊያቀልለት እንደሚችል ይታመናል። እንደ ይሁን እንዳሻው አይነት የውድድር አመቱን በጥሩ አቋም ያጠናቀቀ ተጫዋች መኖሩ ደግሞ ሂደቱን ለማፋጠን የሚረዳ ነው። ፊት መስመር ላይ የተደረጉት ዝውውሮች ደግሞ ከሀገር ውጪ በሚመጡ ተጫዋቾች ላይ ያተኮሩ ይመስላሉ። ከምንም በላይ ከ39ኙ የቡድኑ ጎሎች 23ቱን ያስቆጠረው ናይጄሪያዊውን አጥቂ እኪኪ አፎላቢን ቦታ መሸፈን ቀላል እንዳልሆነ አሰልጣኝ ዘማርያምም ይስማማሉ። በሰጡት አስተያየትም ” አምና ጅማ በአጥቂ ክፍሉ ላይ ኦኪኪን የያዘ ቡድን ነበር። ዘንድሮም የፊት መስመሩን ጥንካሬ መልሶ ማግኘት እጅግ በጣም አስፈላጊ ይሆናል። ያንን ለማድረግ በሀገር ውስጥ ዝውውር ብዙ ተቸግረናል። ከውጪ ያመጣናቸውንም በፍጥነት ለመመዘን በአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች መጠቀም ነበረብን።”  ብለዋል። በአጠቃላይ የተደረጉትን ዝውውሮች በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ደግሞ “አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ለእግር ኳስ ቤተሰቡ አዲስ አይደሉም። በነበሩባቸው ክለቦች አቅማቸውን ያሳዩ ናቸው። እንደ ብሩክ ገብረአብ ያሉትን ደግሞ ከታችኛው ሊግ ለማምጣት ሞክረናል። ያላቸውም ልምድ ተጫዋቾቹን እንደቡድን የማዋቀሩን ስራ የሚያቀላጥፈው ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ ባዘዋወርናቸው ተጫዋቾች የተሻለ ቡድን ይዘን እንደምንቀርብ ይሰማኛል።” የሚል ነበር።


የጅማ አባ ጅፋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት ዘግየት ብሎ መስከረም 4 ላይ በአዳማ ከተማ የተጀመረ ነበር። ከ20 ቀናት በኋላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመዲናዋ ዓመታዊ  ውድድር ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ነገ የዚህን ውድድር የደረጃ ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ደግሞ ለአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው መከላከያ ጋር ይገናኛል። የዝግጅት ጊዜው መዘግየት እና ያለውን ተፅዕኖውን በተመለከተ አሰልጣኝ ዘማሪያም ሲናገሩ ” ያለፈው ዓመት ቡድን አብዛኞቹ ተጫዋቾች የአንድ ዓመት ውል ስለነበራቸው ተበትነዋል። በነበረን አጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም እና በቶሎ ብቁ መሆናቸውን መመዘን ይጠበቅብንም ነበር። የዝግጅት ጊዜያችን በጣም አጭር ነው ፤ ነሀሴ አጋማሽ ላይ ብንጀምር የተሻለ ይሆን ነበር። በሃያዎቹ ቀናት በአራቱ የስልጠና ክፍሎች (ቴክኒክ ፣ ታክቲክ ፣ አካል ብቃት እና ሥነ ልቡና) ቡድንን አዘጋጅቶ ወደ ውድድር መግባት አስቸጋሪ ነው። በተቻለ መጠን ግን ሁሉንም እያፈራረቅን ለመሄድ ሞክረናል። በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻሎችን ማየታችን ጥሩ ተስፋ ሆኖናል። ”  ይላሉ።
በእግር ኳስ ሁሌም ቢሆን ከቻምፒዮንነት ቀጥሎ የሚመጣው የውድድር ዓመት ከባድ ይሆናል። ቡድኑ በተጋጣሚዎች የሚሰጠው ግምት ከፍ ማለት እና ደጋፊው የሚጠብቀው የውጤት ቀጣይነትም አሰልጣኞች ላይ ጫና ሲያሳድር ይስተዋላል። በነዚህ እውነታዎች ላይ ደግሞ የተጫዋቾች በብዛት መልቀቅ ሲጨመርበት በአዲስ መልክ ኃላፊነቱን ለተረከቡ አሰልጣኞች ፈተናውን ከፍ ማድረጉ አይቀርም። አሰልጣኝ ዘማርያም በአንፃሩ ሁኔታው ያሳሰባቸው አይመስልም ” እኔ እንደ አሰልጣኝ የሚያሳስበኝ ቡድኑ መበተኑ ሳይሆን ደጋፊው ቢበተን ኖሮ ነበር። ደጋፊው እስካለ ድረስ ቡድን መገንባት እንደሚቻል ነው የማምነው። ያለን ድንቅ ደጋፊ አሁንም አብሮን መኖሩ ለኛ ትልቅ ብርታት ይሆነናል። ” የሚለው ሀሳባቸው ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።


በአሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ስር የነበረው አባ ጅፋር በአማካይ ክፍሉ በሚገባ የሚታገዝ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል የነበረው እንዲሁም ወጥ የሆነ አሰላለፍን የሚከተል ሆኖ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ ብቃት የተላበሰ ነበር። ዘንድሮ ግን ከዚህ የተለየ አይነት አባ ጅፋር ልናይ እንደምንችል የመጨረሻው የአሰልጣኙ አስተያየት ይጠቁማል። “ቡድኑ ከባለፈው ዓመት የተለየ ቅርፅ ይኖረዋል። ባለፈው ዓመት ፊት ላይ አስፈሪ አጥቂ ስለነበረው ረጃጅም ኳሶችን የሚጠቀም ቡድን ነበር። አሁን ግን በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ እና ተጭኖ የሚጫወት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የሚደርስ ቡድን ነው በመገንባት ላይ የምንገኘው። እስካሁንም እንዳየነው የቡድኑ ቅርፅ ከባለፈው ዓመት የተለየ እንደሆነ ነው።”
ጅማ አባ ጅፋር ነገ በአዲስ አበባ ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃን ለማግኘት ከመከላከያ ጋር የሚጫወት ሲሆን ማክሰኞ ደግሞ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በድጋሜ ከመከላከያ ጋር ይፋለማል። ጥቅምት 17 በሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም የመጀመሪያ ጨዋታውን አዳማ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ያከናውናል።