13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ በሁለት የመዝጊያ ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ቡና ለአራተኛ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።
ሠናይ መስማት የተሳናቸው የእግር ኳስ ክለብ አርቲስቶችን 1-0 ባሸነፉበት ጨዋታ የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቀን ውሎ በተለያዩ የሰርከስ ትርዒቶች ታጅቦ የደረጃ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች ተስተናግደውበታል።
09፡10 ላይ ሦስተኛ ደረጃን ለማግኘት የተገናኙት የጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ ጨዋታ በውድድሩ እስከ መለያ ምት የዘለቀ ብቸኛው ጨዋታ ሆኗል። ተጋጣሚዎቹ እስካሁን ዕድል ባልሰጧቸው ተጫዋቾች ወደ ሜዳ በገቡበት ጨዋታ አዲሱ የጅማ አባ ጅፋር ፈራሚ ማማዱ ሲዲቤ በ19ኛው እና 83ኛው ደቂቃ ላይ የአጨራረስ ብቃቱን ባሳየባቸው ጎሎች ቡድኑን ሁለት ጊዜ መሪ ማድረግ ቢችልም መከላከያዎችም መልስ ከመስጠት አልቦዘኑም። 73ኛው ደቂቃ ላይ ከተስፋ ቡድን ያደገው ይታጀብ ገብረማርያም ተቀይሮ ገብቶ ፤ አዲስ ፈራሚው ዳዊት ማሞ ደግሞ 86ኛው ደቂቃ ላይ በቅጣት ምት ለጦሩ ማስቆጠር ችለዋል።
ጨዋታው 2-2 በመጠናቀቁ ከተሰጡት አምስት አምስት የመለያ ምቶች ውስጥ የመከላከያዎቹ በኃይሉ ግርማ እና ሳሙኤል ታዬ ሲስቱ በአባ ጅፋር በኩል ከኄኖክ ገምቴሳ ውጪ የተቀሩት መቺዎች ማስቆጠር ችለዋል። የውድድሩ ተጋባዥ የሆነው ጅማ አባ ጅፋርም በመለያ ምቶቹ 4-3 በሆነ ውጤት አሸንፎ ሦስተኛ ደራጃን ማግኘት ሲችል ማሊያዊው የፊት መስመር ተሰላፊ ማማዱ ሲዲቤ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
በመቀጠል በኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ መካከል የተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ፣ የባህርዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየው ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዘዳንት ኮ/ል ዐወል አብዱራሂም እና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በክብር እንግድነት የተገኙበት ነበር። በውጤቱም ኢትዮጵያ ቡና 4-1 በማሸነፍ የከተማዋን ዋንጫ ለአራተኛ ጊዜ ማንሳት ችሏል።
በጨዋታው ባህርዳር ከነማዎች በግማሽ ፍፃሜው የተጠቀሙበትን ቡድን ይዘው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ግን በተመስገን ካስትሮ እና አማኑኤል ዮሃንስ ምትክ ክሪዚስቶም ንታንቢ እና ካሉሻ አልሀሰንን በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ አካተዋል። ከሰሞኖቹ የውድድሩ ጨዋታዎች አንፃር ሲታይ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ ፉክክር የታየበት ይህ የፍፃሜ ጨዋታ ስታድየሙን የሞሉት ደጋፊዎች ድምቀት የተለየው ግን አልነበረም።
የጨዋታው አሸናፊ የሆኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሦስቱን ግቦች ያገኙት ከእረፍት በፊት ነበር። 10ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ነስሩ በግራ በኩል ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ኋላ የመለሰለትን ኳስ አልሀሰን ካሉሻ የመጀመሪያ ግብ አድርጎታል። አምና በኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚታወቅበትን ድንቅ ብቃት መድገም የቻለው ካሉሻ አቡበከርን እና ሉኩዋን ከግብ ጠባቂ ጋር ያገናኘባቸው ቅፅበቶች ለቡድኑ ግልፅ የግብ አጋጣሚን ቢፈጥሩም የመጀመሪያው በግቡ ቋሚ ሁለተኛው ደግሞ በምንተስኖት አሎ ጥረት ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ቀጣዮቹ ሁለት ግቦች በሳምሶን ጥላሁን እና አቡበከር ነስሩ የፍፁም ቅጣት ምቶች የተገኙ ነበሩ። ከሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምቶች የመጀመሪያው የመሀል ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጄ አህመድ ረሺድን በክርኑ በመማታቱ ቀጣዩ ደግሞ አቤል ውዱ በሉኩዋ ሱሌይማን ላይ በፈፀመው ጥፋት ምክንያት የተሰጡ ነበሩ።
በግርማ ዲሳሳ እና ፍቃዱ ውርቁ አማካይነት የሚሰነዝሩት የወትሮው የመስመር ጥቃት ተቀዛቅዞባቸው የታዩት ባህርዳር ከተማዎች 21ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት በግራ መስመር በኩል ቶማስ ስምረቱን አልፎ ከዋቴንጋ ጋር ፊት ለፊት ከተገናኘ በኋላ የሞከረው ኳስ ወደ ላይ የወጣበትን አጋጣሚ ብቻ ነው በመጀመሪያው አጋማሽ የፈጠሩት። ይልቁኑም ሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምቶች ያለአግባብ ነው የተሰጠብን በማለት ከኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ጋር የጀመሩት ሰጣ ገባ እስከ ሁለተኛው አጋማሽ ድረስ ዘልቆ ለቡድን መሪው እንዲሁም ለዋና አሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸው ከሜዳ መሰናበት ምክንያት ሆኗቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ባህር ዳር ከተማዎች በተሻለ መልኩ በኢትዮጵያ ቡና የሜዳ አጋማሽ ላይ የመገኘት ዕድል ነበራቸው። ያደረጓቸው ስድስት ቅያሪዎችም ቡድኑ ከመጀመሪያው የተሻለ ሙከራዎችን እንዲያደርግ ግብም እንዲያስቆጥር ረድተዋል። ከነዚህም ውስጥ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ተቀይሮ የገባው ወሰኑ ዓሊ ከሳጥን ውጪ መተው ለጥቂት ወደ ውጪ የወጡት ኳሶች ይጠቀሳሉ። 74ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛው ተቀያሪ እንዳለ ደባልቄ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ በመምታት ያስቆጠራት ድንቅ ግብ ደግሞ ልዩነቱን ወደ 3-1 ዝቅ ያደረገች ነበረች።
አቡበከር ነስሩ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶባቸው ሁለተኛዉን አጋማሽ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎችም አራት ቅያሪዎችን አድርገዋል። ቡድኑ በፍጥነት ወደ ጎል በመቅረብም በአልሀሰን ካሉሻ እና ሉኩዋ ሱሌይማን አማካይነት ተጨማር ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። ተቀይሮ የገባው ፍፁም ጥላሁን በግራ መስመር ይዞ በመግባት ያሳለፈውን ኳስ ግን አቡበከር በቀላሉ ወደ አራተኛ ጎልነት ለውጦታል። በባህር ዳሮች በኩል ኢስማ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የተላከን ኳስ በአግባቡ ሳያርቀው አግኝቶ ደረጄ መንግስቱ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረብም ሙከራው ለጥቂት በጎን ወጥታለች። ጨዋታውም በዚህ መልኩ አቡበከር ነስሩን ኮከብ አድርጎ በኢትዮጵያ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የፍፃሜው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ በነበረው ፕሮግራም ውድድሩን ከአንድ እስከ ሶስት ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ ቡና ፣ ባህርዳር ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር የሜዳሊያ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። የኢትዮጵያ ቡናዋቹ አቡበከር ነስሩ እና ሉኩዋ ሱሌይማን እንዲሁም የአዳማ ከተማው በረከት ደስታ በእኩል ሦስት ጎሎች የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢዎች በመሆን ሲሸለሙ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ዳንኤል ደምሴ እና አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ኮከብ ተጨዋች እና አሰልጣኝ ሆነዋል። በተጨማሪ ሽልማቶች ባህርዳር ከተማ የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ ፤ የቡድኑ የመስመር አጥቂ ግርማ ዲሳሳ ደግሞ የምርጥ ግብ አስቆጣሪነት ሆነዋል። ከመስከረም 26 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውን 13ኛውን የመዲናዋን ውድድር ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡናም የዋንጫ ሽልማቱን ተቀብሏል።