በነሀሴ 2020 የጃፓኗ መዲና ቶኪዮ የምናስተናግደው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የእግርኳስ ዘርፍ በአህጉራት ተከፋፍለው በሚደረጉ የ23 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ በሚመዘገቡ ውጤቶች መሰረት በሚያልፉ ሀገራት መካከል ይከናወናል።
ጃፓንን ጨምሮ 16 ሀገራት በሚሳፉበት የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የወንዶች እግርኳስ አፍሪካ ሶስት ሀገራትን የሚያሳትፍ ኮታ ያላት ሲሆን ቡድኖችን ለመለየት ከ6 ወራት ቀደም ብሎ የሚከናወን የ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ይከናወናል። ይህ ውድድር በታህሳስ ወር 2019 በግብፅ አስተናጋጅነት ሲከናወን በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ሶስት የማጣርያ ዙሮች ይኖሩታል። ቶኪዮ ለመገኘት ረጅም ጉዞ የሚጠይቀው ይህ ውድድር ማጣርያ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሶማሊያ ጋር ያደርጋል ።
ኢትዮዽያ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታዋን በአዲስ አበባ ስቴዲየም ህዳር አምስት (ኖቬምበር 14) ስታደርግ የመልሱ ጨዋታ ከኖቬንበር 18-20 (ከኅዳር 9-11) ይከናወናል። የመልሱ ጨዋታን በሶማሊያ ለማድረግ አስተማማኝ ፀጥታ ባለመኖሩ ምክንያት በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታው እንዲደረግ ካፍ በመወሰኑ ሶማሊያ ገለልትኛ ሜዳዋን በቅርቡ ታሳውቃለች ተብሎ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ጅቡቲ ተመራጭ ሀገር ልትሆን እንደምትችል ተገምቷል።
ኢትዮጵያ በድምር ውጤት አሸናፊ ከሆነች በቀጣይ የማጣርያ ዙር ከማሊ ብሔራዊ ቡድን ጋር በመጋቢት ወር ላይ በደርሶ መልስ ስትጫወት ይህንን ዙር በብቃት ከተወጣች በመጨረሻው ዙር ከሩዋንዳ፣ ሞሮኮ እና ኮንጎ ዲ.ሪ. አንዳቸውን የምታገኝ ይሆናል። ኢትዮጵያ ይህን ዙር ካለፈች ወደ አፍሪካ ዋንጫው የመቀላቀል እድል ስታገኝ በውድድሩ ከ1-3 ከወጣች ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ታመራለች።
ጥቂት እውነታዎች ስለ ኢትዮጵያ እና የኦሎምፒክ እግርኳስ
ኢትዮጵያ በኦሎምደፒክ ጨዋታዎች አትሌቲክስን ተጠቅማ ብዙ ታሪክ ብታስመዘግብም በእግርኳስ ግን ተሳትፋ አታውቅም። በ2016 በሪዮ ዲጄንየሮ እንዲሁም በ2012 በለንደን በተስተናገደው ውድድር ማጣርያዎች ላይ ያልተሳተፈች ሲሆን በ2008 የቤይጂንግ ኦሎምፒክ እስከ ምድብ ማጣርያ ደርሳ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በሜዳዋ አቻ ከተለያየች በኋላ በወቅቱ በፊፋ በተጣለባት እገዳ ምክንያት ከጋና እና ናይጄርያ ጋር ጨዋታ ሳታደርግ ከውድድሩ ወጥታለች።
ከ1956 የሜልቦርን ኦሎምፒክ ጀምሮ በእግርኳስ ማጣርያዎች እየተሳተፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ በሁለት አጋጣሚዎች ለማለፍ በእጅጉ ተቃርባ ነበር። በመጀመርየ የማጣርያ ተሳትፎዋ በግብፅ 9-3 ድምር ውጤት ብትሸነፍም ግብፅ ከውድድር ራሷን በማግለሏ ለኢትዮጵያ የመሳተፍ እድል ተፈጥሮላት የነበረ ቢሆንም ለውድድሩ ዝግጁ ባለመሆኗ ሳትሳተፍ መቅረቷ በታሪክ ተመዝግቧል። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሥዩም አባተ የተመራው ብሔራዊ ቡድን በ2004 የአቴንስ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ከሞሮኮ፣ ዩጋንዳ እና አንጎላ ጋር ተደልድሎ ከሁሉም ሀገራት የበለጠ የማለፍ ዕድል ይዞ የመጨረሻ ጨዋታውን ቢያደርግም በዩጋንዳ 2-1 ተሸንፋ ሞሮኮ ደግሞ አንጎላን በማሸነፏ ሳያልፍ ቀርቷል።
የሴቶች እግርኳስስ?
የእድሜ ገደብ የሌለው የሴቶች እግርኳስ ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሪዮ 2016 ማጣርያ ላይ አልተሳተፈም። በቀደመው (ለንደን 2012) ደግሞ በኮንጎ ዲ.ሪ 3-0 ድምር ውጤት ተሸንፎ ከመጀመርያው ዙር ተሰናብቷል። የማጣርያው አካሄድ ያልታወቀበት ይህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ስለመሳተፏ የታወቀ ነገር የለም።