በክረምቱ የዝውውር መስኮት በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የኮከብ ግብ አስቆጣሪው ኦኪኪ አፎላቢ መልቀቅ የፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈን የሚያደርገውን ጥረት በመቀጠል ማሊያዊው ማማዱ ሲዲቤን በእጁ አስገብቷል።
ማማዱ ሲዲቤ በአባጅፋር የአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ ሲያሳልፍ በአዲስ አበባ ዋጫ ላይ በግማሽ ፍፃሜ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በተደረገው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ለመጀመርያ ጊዜ መጫወት ችሏል። ትላንት ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ መከላከያ ጋር ሁለት ግቦችን በስሙ በማስመዝገብ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ መመረጡ የሚታወስ ነው። በውድድሩ ላይ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠ ብቸኛው የውጪ ዜጋም ሆኗል። በአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜው እንዲሁም በሲቲ ካፑ ላይ ካሳየው አቋም በመነሳት አባ ጅፍሮች የአጥቂ ክፍላቸውን ክፍተት እንደሚደፍን ተማምነዋል።
የ25 ዓመቱ አጥቂ በሀገሩ ክለብ ኤኤስ ፖሊስ እስከ 2014 የቆየ ሲሆን በዚሁ ዓመት በአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ከተሳተፈ በኋላ ወደ ሞሮኮ በማምራት በቦቶላ ሊግ በሚሳተፉት ኦሎምፒክ ኮሪብጋ፣ ሲኤ ኬኒፍራ፣ ራቻድ ቤርኖሲ እና ራፒድ ኦዌድዜም ክለቦች ተጫውቷል።
ማማዱ ሲዲቤ ከዚህ ቀደም ከቡድኑ ጋር የፕሪምየር ሊጉ ባለድል የነበሩት ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ እና የሀገሩ ዜጋ አዳም ሲሶኮ እንዲሁም አዲስ ፍራሚዎቹ ዲድዬ ለብሪ እና ቢስማክ አፒያ እና ማማዱ ሲዲቤ አምስተኛው የቡድኑ ተጫዋች ሆኖ ተመዝቧል።