በሴቶች እግርኳስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠንካራ እና ውጤታማ ቡድን የነበረውና የ2010 ቻምፒዮኑ ደደቢት የሴቶች እግርኳስ ቡድን ክለቡ ባጋጠመው የፋይናንስ ችግር ምክንያት በዘንድሮ ዓመት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ የማይሳተፍ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።
የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ይህን ብለዋል። ” ክለቡ የቦታ ለውጥ (ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ) ማድረጉን ተከትሎ እና የክለቡ ባጋጠመው የፋይናስ ችግር ምክንያት የወንድ እና የሴት ቡድኑን ይዞ መጓዝ ስለሚቸገር የሴቶች ቡድን ዘንድሮ አይኖረንም። የፋይናስ ችግሩ ሲስተካከል በቀጣይ የሚያስፈልገውን ነገር አሟልተን ወደ ነበርንበት ተፎካካሪነት እንመለሳለን ብለን እናስባለን። በሴቶች እግርኳስ እድገት ላይ ያለፉትን ዓመታት የቻልነውን ነገር ሁሉ ሰርተናል። ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የሴቶች ቡድን ዘንድሮ አይኖረንም። ለኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይንን ጉዳይ በደብዳቤ አሳውቀናል” ብለዋል
በ2003 ምስረታውን ያደረገው የደደቢት የሴቶች ቡድን 2004 በአሰልጣኝ አስራት አባተ እየተመራ የሊጉን የመጀመርያ ዋንጫ አንስቷል። ከ2005-2007 በዋንኛ ተቀናቃኙ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ተቀድሞ ዋንጫውን ቢያጣም ከ2008-2010 በተከታታይ ለ3 ዓመታት ቻምፒዮን በመሆን በአጠቃላይ በ4 ዋንጫዎች ቀዳሚነቱን ይዟል።
የደደቢትን ከውድድር መውጣት ተከትሎ ኅዳር አንድ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በ11 ክለቦች ይቀጥላል ወይስ በደደቢት ምትክ አንድ ክለብ ተጨምሮ በ12 ቡድኖች መካከል ይከናወናል የሚለው ጉዳይ ተከታትለን ይዘንላችሁ እንቀርባለን።