የአስቻለው ግርማ ማረፍያ ሀዋሳ ከነማ ሆኗል

የ2007 የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚው ሀዋሳ ከነማ የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አጥቂ አስቻለው ግርማን የግሉ አድርጓል፡፡

ከኢዮጵያ ቡና ጋር የነበረው ውል ከተጠናቀቀ በኋላ ስሙ በተለይም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲያያዝ የከረመው አስቻለው በመጨረሻም ለአንድ አመት ለደቡቡ ክለብ ለመጫወት ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ ወርሃዊ 62ሺህ ብር ይከፈለዋልም ተብሏል፡፡

የሀዋሳ ከነማው አሰልጣኝ በዝውውሩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት አስቻለው ለክለቡ ለመጫወት ተስማምቷል፡፡ ‹‹ ባለኝ መረጃ መሰረትበቃል ደረጃ ተስማምተናል፡፡ ዛሬ ፊርማውን ያኖራል፡፡ በፌዴሬሽን ተገኝቶ በይፋ ሲፈራረም ነው ሁሉንም ነገር መናገር የምንችለው›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

በባሌ ከተማ የተወለደው አስቻለው ግርማ በ2005 አጋማሽ ከሱሉልታ ከነማ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከተሸጋገረ በኋላ በየአመቱ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት በሀገሪቱ ከሚጠቀሱ ምርጥ የመስመር አጥቂዎች ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል፡፡

 

 

ተጨማሪ መረጃዎች – ኑራ ኢማም

ያጋሩ