ወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ ወልቂጤ ከተማን ለቆ ሀዋሳ ከተማን በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሏል፡፡
በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ አማካኝነት በ2009 ክረምት ወር ላይ በሀዋሳ ቄራ ተብሎ በሚጠራበት ሜዳ በሚደረግ የታዳጊዎች ውድድር ላይ የተገኘው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ብሩክ በየነ በወቅቱ የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ የነበረው የአሁኑ የሀዋሳ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ተመልምሎ የ2010 የውድድር አመትን በወልቂጤ አሳልፏል፡፡ ተጫዋቹ በከፍተኛ ሊጉ 6 ጎሎች በማስቆጠር የክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የአንድ ዓመት የወልቂጤ ውሉን አጠናቆ ከአንድ ወር በላይ የሙከራ ጊዜን በሀዋሳ አሳልፎ አሳማኝ እንቅስቃሴን በማሳየቱ በሁለት ዓመት ውል ሀይቆቹን ተቀላቅሏል፡፡
በተያያዘ ዜና ከቀናት በፊት ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሎ የነበረው መሐመድ ናስር ሁለት ቀን ከቡድኑ ጋር ልምምድ ከሰራ በኋላ በስምምነት መለያየቱ ታውቋል፡፡