በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከረጅም ጊዜ በኋላ የተመተለሰው ደቡብ ፖሊስ በአጥቂ ስፍራ ላይ ያለውን መሳሳት ለመቅረፍ ልዑል ደረጄ የተባለ ተጫዋች በአንድ ዓመት ውል አስፈርሟል። ፈጣኑ አጥቂ ወደ ደቡብ ፖሊስ ከማምራቱ ቀደም ብሎ በአንደኛ ሊጉ ክለብ ሐረር ሲቲ አሳልፏል።
ትላንት በተዘጋው የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ወደ ደቡብ ፖሊስ ያመራው ተጫዋች የጋና ዜግነት ያለው ኢሳህ ሀዘይፋ ነው። የ22 ዓመቱ የአጥቂ አማካይ ስፍራ ተጫዋች የአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ነው ለክለቡ ፊርማውን ያኖረው። አማካዩ በጋና ሊግ ተሳታፊ በነበረው ኸርትስ ቤቢስ እንዲሁም ያለፉትን ሶስት የውድድር ዓመታት ደግሞ ወደ ጋቦን አምርቶ ፔሊካን በመጫወት አሳልፏል። በ2017 የጋና ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አባልም ነበር።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና አንጋፋውን ኬኒያዊ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ውሉ እንዳራዘመ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ከክለቡ ጋር ተለያይቶ የቀድሞ አሰልጣኙን ግርማ ታደሰን ተከትሎ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ማምራቱ ታውቋል።