በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት ዙሪያ የምናደርገው ዳሰሳ አጼዎቹን ያስመለክተናል።
በ2009 ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጎ ለሦስተኛ የውድድር ዓመቱ እየተዘጋጀ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በመጣበት ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ ችሏል። በተለይም ክለቡ እስከ 11ኛው ሳምንት ድረስ አንድ ሽንፈት ብቻ ያስተናገደበት የመጀመሪያ ዓመት የመጀመሪያ ዙር ጉዞው መልካም የሚባል ነበር። አስራ አንድ ተጫዋቾችን አስፈርሞ ከአሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ ጋር ወደ ውድድር የገባበት 2010ም ተመሳሳይነት ያለው ውጤት የተመዘገበት ቢሆንም በመሀል ያሳየው መቀዛቀዝ ዓመቱ ሊጠናቀቅ አራት ወራት ሲቀሩት የአሰልጣኝ ለውጥ እንዲያደርግ ያስገደደ ነበር። የመጨረሻዎቹን አስራ ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑን የመሩት የቀድሞው የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እስከ ፕሪምየር ሊጉ መገባደጃ ድረስ ቆይተው የቡድኑን ውጤት ለማቃናት በተረከቡት ኃላፊነት በአራት ድል ፣ በአራት ሽንፈት እና በአራት የአቻ ውጤቶች ከፋሲል ጋር የነበራቸውን ጊዜ አጠናቀዋል። ከካቻምናው ደረጃቸው በአንድ ዝቅ ብለው በሰባተኝነት የጨረሱት አፄዎቹ 10 ጨዋታዎችን አሸንፈው እንዲሁም 11 ጊዜ ተረተው በ41 ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው በስድስት በመራቅ ነበር 2010ን የጨረሱት። ቡድኑ ደካማ በነበረው የጎል ማስቆጠር ሂደቱ ከወልዲያ እና ድሬዳዋ ቀጥሎ ዝቅተኛውን ቁጥር (22) ያስመዘገበ ሲሆን በአንፃሩ 28 ግቦችን አስተናግዷል።
ሐምሌ ከገባ በኋላ ውላቸውን ከጨረሱት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር እንደማይቀጥል የታወቀው ፋሲል በሀዋሳ ከተማ ዓመቱን ያሳለፉት አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ቀጥሯል። በአሰልጣኙ ቅጥር ዙሪያ በኢትዮጵያ ሆቴል በተሰጠው መግለጫም ክለቡ ‘ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ’ በሚለው ስያሜ እንደሚጠራ እንዲሁም በርካታ የመዋቅር ለውጦችን እንደሚያደርግ ተገልፆ ነበር። ፋሲሎች ከአሰልጣኝ ቅጥሩ በኋላ በፍጥነት ነበር ወደ ዝውውር መስኮቱ የገቡት። በሂደትም ከክለቡ የለቀቁ ከድር ኸይረዲን ፣ ይስሀቅ መኩሪያ ፣ ኄኖክ ገምቴሳ ፣ ራምኬል ሎክ ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ ፣ ሙሉቀን አቡሀይ ፣ ናትናኤል ጋንቹላ ፣ መሀመድ ናስር ፣ ሱለይማን አህመድ ፣ ሰንደይ ሙቱኩ ፣ ሀሚስ ኪዛ እና ፍሊፕ ዳውዝ የተውትን ክፍተት ለመሙላት እስካሁን ዘጠኝ የሀገር ውስጥ እና ሦስት የውጪ ዜጋዎችን ማስፈረም ችሏል።
“ከተጫዋቾች ፍላጎት እና ከክለቦች አቅም አንፃር ሁሉም አሰልጣኝ በዝውውር ሂደት ውስጥ የሚፈልጋቸውን ተጫዋቾች ሁሉ አያገኝም። እንደውም እኛ ቀድመን ወደ ገበያው በመውጣታችን ከሌሎች ክለቦች ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ነው ነባሮቹንም ማቆየት አዳዲሶችንም ማምጣት የቻልነው። በጥቅሉ ሲታይም የምንፈልጋቸው ዓይነት ተጫዋቾች አግኝተናል ብዬ ነው የማስበው። ከምንም በላይ አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸው እና ከኳስ ጋር ጥሩ መሆናቸው ዝውውሮቻችንን ስኬታማ ያደርጋቸዋል።” ይላሉ የቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ክለባቸው ባጠናቀቀቻው ደደቢት ፣ አዳማ እና ድሬዳዋ ላይ ያተኮሩ የሚመስሉት አስራሁለት ዝውውሮች ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡ። ፋሲል ከነማ ሰለሞን ሀብቴ (ተከላካይ/አማካይ) ፣ ከድር ኩሊባሊ (ተከላካይ/አማካይ) እና ሽመክት ጉግሳን (አማካይ) ከደደቢት ፤ ሱራፌል ዳኛቸው (አማካይ) እና ሙጂብ ቃሲምን (ተከላካይ) ከአዳማ ከተማ ፣ ጀማል ጣሰው (ግብ ጠባቂ) እና ዮሴፍ ዳሙዬን (አማካይ) ከድሬዳዋ ከተማ ፣ ሀብታሙ ተከስተን (አማካይ ከመቐለ ከተማ) እና በዛብህ መለዮን (አማካይ ከወላይታ ድቻ) እንዲሁም ፋሲል አስማማውን (አጥቂ ከለገጣፎ ) ያስፈረመ ሲሆን ሁለቱ ናይጄሪያዊያን አጥቂዎች ኢዙ አዙካ እና ኢፌኒ ኤድም ቡድኑን ተቀላቅለዋል።
በአሰልጣኞች ቡድን ዙሪያ በተጫዋቾች ዝውውር መካከል ክለቡ ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ረዳት እንዲሆኑ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እና ኃይሉ ነጋሽ በምክትል አሰልጣኝነት ሾሟል። ወጣት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደግ እና ማብቃት የሚለው ኃላፊነት በቅጥሩ ወቅት የተሰጣቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዘንድሮው ቡድናቸው ውስጥ ሰባት ተጫዋቾችን ለማካተት ሀሳቡ አላቸው። ” ሰባት ተጫዋቾችን ከታችኛው ቡድን እና በአካባቢው ካሉ ከተሞች አምጥተናል። ከኛ ጋር ባደረጉት ዝግጅትም ባሳዩት አቋም ተቀብለናቸዋል። የሚቀረው ዕድሜያቸውን ለማረጋገጥ በፌዴሬሽኑ በኩል የሚደረገው ምርመራ ነው። ያንን ማለፍ ከቻሉ ባሳዩት አቋም ደስተኞች ነን። ዋናውን ቡድን እንዲቀላቀሉም ሂደት ላይ እንገኛለን። በአረንጓዴ ቴሴራ ሃያ ሶስት ተጫዋቾችን በመያዛችን መመዘኛውን ካሟሉ ለሁሉም የሚሆን ቦታ አለን።”
የፋሲል ከነማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ባህርዳር ላይ ነሀሴ 20 በብሔራዊ ቡድን ምርጫ እና በጉዳት ምክንያት ካልነበሩት ውጪ 26 ተጫዋቾችን በመያዝ በጂም እና በሜዳ ላይ ስራዎች የጀመረ ነበር። ቡድኑ ለአንድ ወር በባህርዳር በቆየበት ጊዜም ከመደበኛው ልምምዱ በተጨማሪ ከዳንግላ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጓል። በመቀጠል ወደ መዲናዋ በመምጣት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል። በውድድሩ ሦስት የምድብ ጨዋታዎችን አድርጎ ቢወጣም ተሳትፎው ተጫዋቾችን ለማየት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው አሰልጣኝ ውበቱ ተናግረዋል። በቀጣይ ቀናትም ምንም እንኳን በአዲስ አበባ የሜዳ ችግር ቢያጋጥመውም ጥቂት ቀናትን በመቆየት ከኢትዮጵያ መድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጨማሪ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች በማድረግ ከሲዳማ ቡና ጋር ሀዋሳ ላይ ላለበት ጨዋታ ለመዘጋጀት ወደ ዝዋይ አምርቷታል። በድምሩም ፋሲል ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ሰባት ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል።
ፋሲል አዲስ ያመጣቸው ተጫዋቾች ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ የፈራሚዎች ቁጥር መበራከት በራሱ ቡድንን እንደ አዲስ ወደ መግንባት ሂደት ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው። አሰልጣኙም አዲስ ሲሆን ደግሞ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ በትውውቅ ላይ እንዲያተኩር ያስገድዳል። የተረጋጋ የቡድን ስብስብ ይዞ ከመቀጠል ጋር ሲነፃፀር በዝግጅት ወቅት የሚኖረው የቡድን ግንባታ ሂደት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው መገንዘብ ይቻላል። አሰልጣኝ ውበቱ ከዚህ ጋር በተገናኘ በሰጡት አስተያየትም ” በዝግጅታችን ወቅቱ ሁሉንም ነገሮች ለመዳሰስ ሞክረናል። በዋነኝነት ግን እኔም አዲስ ከመሆኔ እና በርካታ አዳዲስ ፈራሚዎች ከመኖራቸው አንፃር እነሱ ጋር ያለውን ነገር ለማወቅ እና እኔ የምፈልጋቸውንም ነገሮች በነሱ ውስጥ ለማስረፅ ስራዎችን እየሰራን ነው። ለዚህም ከሜዳ ላይ በተጨማሪ በክፍል ውስጥም እየተገናኘን እየተነጋገርን እንገኛለን። ” ብለዋል። አሰልጣኙ ስለጠቅላላው የቡድን ግንባታቸው የሰጡት አስተያየት ደግሞ ” ቡድን የሚገነባው ቀስ በቀስ ነው። የመጡት አስራ ሦስት ተጫዋቾችም ሆኑ ነባሮቹ እኔ ከምፈልገው ነገር ጋር አብረው መሄዳቸው በሂደት ነው የማየው። የመቀበል ፍጥነታቸው የተለያየ በመሆኑ በሂደት ወደ ምንፈልገው ነገር የምንመጣ ይመስለኛል። እንደ ክፍተት የተመለከትኩት ተጫዋቾቹ ያላቸው ብቃት እንዳለ ሆኖ መሀል ሜዳ ላይ ልምድ ያለው እና ጨዋታን መቆጣጠር የሚያስችል ባህሪ የተላበሰ አማካይ በቡድኑ ውስጥ አለመኖሩ በጨዋታዎች ላይ በጣም የመቻኮል እና ጥድፊያን እንድናይ አድርጎናል። ” ብለዋል።
ፋሲል ከነማ በሊጉ በቆየባቸው ሁለት ዓመታት በተለይም ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ላይ በጥቂቱ ኳስ ለመቆጣጠር ሲሞክር ቢታይም በአመዛኙ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ጎል ለመድረስ የመሞከር አዝማሚያን ያሳያል። ኳሶችን በፍጥነት ለመስመር አጥቂዎች በማድረስ ላይ በተመረኮዘው አጨዋወቱም የኳስ ቁጥጥር ላይ በቂ ትዕግስት ሲያሳይ አይታይም። በሌላ በኩል አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚሰሯቸው ቡድኖች ለረጅም ደቂቃዎች ኳስን ተቆጣጥረው ለመቆየት የሚሞክሩ ናቸው። በመሆኑም ዘንድሮ ፋሲል ከነማ ለወጥ ያለ መልክ ሊኖረው እንደሚችል መገመት ይቻላል። የአሰልጣኙ የመጨረሻ አስተያየትም ይህንን ያመለክታል። ” ዋናው የአጨዋወት መንግዴ አይቀየር እንጂ ሁልጊዜም የተሻሉ አዳዲስ ነገሮች መጨመራቸው አይቀርም። አሁንም በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ የተመሰረተ ቡድን ነው እንዲኖረኝ የምፈልገው። በወጣቶች የተገነባ ቡድን በመሆኑም የጨዋታ ፍጥነታችን እንደሚጨምር አስባለው። ነገር ግን ፍጥነታቸውን የሚቆጣጠሩበት መንገድ ላይ ነው አሁን ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው። ያ ከሆነ የሚያዝናና እና ወደ ፊት ተጭኖ የሚጫወት ቡድን እንደሚኖረን ማሰብ ይቻላል። ነገር ግን ይሄን በምን ያህል ጊዜ እናሳካዋለን የሚለው በተጫዋቾቹ የመቀበል አቅም ላይ የሚመሰረት ይሆናል። የጊዜ አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ ጥሩ ቡድን ይዘን እንደምንቀርብ ተስፋ አድርጋለው። ውጤቱም በሂደት እንደሚመጣ አምናለው። ”
በሳምንቱ መጨረሻ በሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማ እንደ 2009ኙ ሁሉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሲዳማ ቡና ጋር በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ከነገ በስትያ የሚያደረግ ይሆናል።