የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ

ወልዋሎ ዓአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት ዳሰሳችን ባለተራ ነው።

ባለፈው ዓመት ወደ ሊጉ አድጎ ሁለት የተለያየ መልክ ያለው የውድድር ጊዜን ያሳለፈው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ሊጉን እስከ መምራት ደርሶ የነበረ ቢሆንም በሜዳው በመከላከያ ከተሸነፈ በኋላ ቀስ በቀስ ተንሸራቶ እስከመጨረሻው ሳምንት ላለመውረድ ሲታገል ለመቆየት ተገዷል። በ2009 በከፍተኛ ሊግ ባሳዩት ወጥ አቋም ዓመቱን ሙሉ ከሊጉ መሪነት ሳይወርዱ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉት ቢጫ ለባሾቹ ወደ ሊጉ ከመጡ በኋላ ከ14 አዲስ ፈራሚዎች ጋር በአሰልጣኝ ብርሃነ ገብረእግዚአብሄር ስር ነበር የውድድር ዓመቱ የጀመሩት። በብዙ መነጋገርያ ርዕሶች ታጅቦ በዘለቀው የመጀመሪያው የሊጉ ዓመታቸው ከአሰልጣኝ ብርሀኔ ጋር በመለያየት ከአሰልጣኝ ሃፍቶም ኪሮስ ቀጥሎም ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ጋር ቀጥለው ውድድሩን ጨርሰዋል። በ35 ነጥቦች ከመውረድ አፋፍ ደርሰው በግብ ልዩነት የተረፉት ወልዋሎዎች 8 ጨዋታዎችን ሲያሸንፉ ከተቀሩት 22 ጨዋታዎች እኩሌታውን በአቻ እኩሌታውን ደግሞ በሽንፈት አገባደዋል።

ለአዲሱ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ቡድን አባላት ላይ ብዙ ለውጥ ያደረጉት ወልዋሎዎች ሃፍቶም አዳነን በቡድን መሪነት ፣ ታደሰ አብርሃን በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝነት ፣ አታክልቲ አለነን ደግሞ በቡድን ሃኪምነት ሾመዋል። ሆኖም ክለቡ ባለፈው ዓመት ቡድኑን በመሀል ተረክበው ከመውረድ ያተረፉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ውል በማራዘም አብሮ ለመቀጠል ወስኗል። ሌላኛው ለውጥ ይሆናል ተብሎ የተጠበቀው የሜዳው ጉዳይ ነበር። አዋራማው የክለቡ ሜዳ አምና በብዙው መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቶ ዘንድሮ ሳር ይለብሳል ተብሎ ቢጠበቅም ስራው እስካሁን አልተገባደደም። ይህን ተከትሎም የመጀመሪያዎቹ የሊግ ጨዋታዎች መቐለ ላይ እንደሚከናወኑ ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ የዓዲግራቱ ክለብ እንደ አብዛኞቹ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በዝውውሩ ብዙ ተሳትፎን ያደረገ ሲሆን ከአስር ተጫዋቾቹ ጋርም ተለያይቷል። ዘውዱ መስፍን ፣ አብርሃ ተዓረ ፣ አለምነህ ግርማ ፣ መኩርያ ደሱ ፣ ከድር ሳሊህ ፣ ወግደረስ ታየ ፣ ማናየ ፋንቱ ፣ አታክልቲ ፀጋይ ፣ ኤፍሬም ጌታቸው እና አሳሪ አልመሃዲ ከክለቡ ጋር እንደማይቀጥሉ የተረጋገጡ ተጫዋቾች ናቸው።

 

አምና እስከ ውድድር ዓመቱ አጋማሽ በሊጉ ጥሩ ፍሰት ያለው ጨዋታ ከሚያሳዩ ቡድኖች ውስጥ መካተት ችለው የነበሩት ወልዋሎዎች ያልተሳካ የዝውውር አካሄዳቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው መናገር ይቻላል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ቡድኑ በዓመቱ መጀመርያ አስፈርሟቸው ከነበሩተጫዋቾች መካከል ከአምስቱ (ብሩክ አየለ፣ ቢንያም አየለ፣ በለጠ ተስፋዬ ፣ እዮብ ወልደማርያም እና ሮቤል ግርማ) ጋር ዓመቱ ሳይጠናቀቅ መለያየቱ ነው። የባለፈውን ዓመት ስህተት ላለመድገም ከማሰብ በመነጨም የዘንድሮዎቹ 11 ፈራሚዎች በሊጉ ባላቸው ልምድ የተመረጡ ይመስላል። ከነዚህም መካከል አስራት መገርሳ (አማካይ) ፣ ደስታ ደሙ (ተከላካይ) ፣ ብርሃኑ ቦጋለ (ተከላካይ) እና ኤፍሬም አሻሞ (የመስመር አጥቂ) ከደደቢት የፈረሙ ናቸው። አማኑኤል ጎበና (አማካይ ከአርባምንጭ) ፣ ዳንኤል አድሃኖም ( ተከላካይ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ) ፣ ሮቤል አስራት (ተከላካይ ከኢትዮጵያ ቡና) ፣ ቢንያም ሲራጅ (ተከላካይ ከጅማ አባጅፋር) ፣ ዳዊት ፍቃዱ ( አጥቂ ከሀዋሳ ከተማ) እና ዓብዱላዚዝ ኬይታ (ጊኒያዊ ግብ ጠባቂ ከ ቢዩልድ ኮን) ደግሞ ቀሪዎቹ ፈራሚዎች ናቸው። የጊኒያዊው ግብ ጠባቂ መምጣትም ክለቡ በሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ከሚጠቀሙ አምስት ክለቦች ተርታ የመሰለፉን ነገር ታሪክ አድርጎታል። በሌላ በኩል በረከት አማረ ፣ ሳምሶን ተካ እና ኤፍሬም ኃይለማርያምን ካሳደጉ በኋላ ባለፈው የውድድር ዓመት ከታዳጊ ቡድናቸው ተጫዋች ያላሳደጉት ወልዋሎዎች ዘንድሮ በረከት ገብረእግዚአብሔር እና ሰመረ ሃፍታይን ወደ ዋናው ቡድን አሳድገዋል።

ክለቡ በዚህ የዝውውር መስኮት ከባለፈው ዓመት በእጅጉ የተሻለ ዝውውር ማድረጉን ዋና አሰልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ” 80% የምንፈልጋቸውን ተጫዋቾች አግኝተናል። ግብጠባቂ ለማስፈረም ብዙ ጥረት አድርገን አሁን የምንፈልገው ብቃት ያሟላ ግብ ጠባቂ አግኝተናል። ከሱ ውጪ አማራጫችንን ሚያሰፋልን የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ፈልገን ነበር ፤ አልተሳካልንም። ነገር ግን በዚህ ዓመት መስራት ለምንፈልገው ቡድን የሚሆኑ ኳስ ተቆጣጥረው መጫወት የሚችሉ እና የመጫወት ፍላጎት ያላቸው ወጣት ተጫዋቾችን አግኝተናል።”

ቀድመው ነሃሴ 21 ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት የገቡት ወልዋሎዎች ዝግጅታቸውን በዓዲግራት እና መቐለ ነበር ያካሄዱት። ስለ ቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው አሰልጣኝ ፀጋየ ኪዳነማርያም ሲገልፁ ” በ 19 እና 20 ተጫዋቾቻን ወደ ካምፕ እንዲገቡ ካደረግን በኋላ እስከ 25 በዓዲግራት ቀለል ያለ ልምምድ አሰርተን ወደ መቐለ ነው ያመራነው። እዚህ ከመጣን በኋላም የትግራይ ዋንጫ እስኪጀመር በመሰረታዊ የአካል ብቃት ስልጠና እና ቡድኑን ለማዋሃድ በሚያግዙን በታክቲክ እና ቴክኒክ ላይ ያተኮሩ ልምምዶችን በቀን ሁለት ጊዜ እያሰራን ነበር የቆየነው። አሁን ግን ውድድሩም እየተቃረበ ስለሆነ ልምምዳችንን በቀን አንዴ አድርገን ቡድኑን ለውድድር ብቁ እያደረግን እንገኛለን” ። ይላሉ።

ከትግራይ ዋንጫ በጊዜ የተሰናበቱት ወልዋሎዎች ተመጣጣኝ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን አለማድረጋቸው በቡድን ግንባታው ብዙም ተፅዕኖ እንደማይኖረውም አሰልጣኙ ያስባሉ። በአስተያየታቸውም “በርግጥ ብዙ ተጫዋቾች እንደ ማስፈረማችን ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ተጨማሪ ሦስት የሚደርሱ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ማድረግ ፈልገን ነበር። እስካሁን ግን ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ነው ያደረግነው። ሆኖም ቡድናችን በፍላጎት እና በጠንካራ ስራ የተመሰረተ ስለሆነ ብዙም ችግር አይኖረውም። ” በማለት ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።

ወልዋሎ ሊጉን ሲቀላቀል በአጫጭር ቅብብሎች ላይ ተመስርቶ የሚያጠቃ ቡድን ነበር። ሆኖም በሂደት ምርጫው ባደረገው አጨዋወት የተጋጣሚን የኋላ መስመር ሰብሮ መግባት እየከበደው ሲሄድ ታይቷል። የውድድር ዓመቱ አስጨናቂ እየሆነ ሲመጣም ቡድኑ በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ፣ ሪቻርድ ኦዶንጎ እና አብዱርሀማን ፉሰይኒ የሦስትዮሽ የፊት መስመር ላይ ብቻ የተመሰረተ እየሆነ መጥቷል። ዘንድሮ ግን ከባለፈው የተለየ አጨዋወት ይዞ እንደሚቀርብም በሚጠቁም መልኩ ከአንድ እስከ አምስት ባለው ደረጃ ውስጥ ለማጠናቀቅ ያቀዱት አሰልጣኝ ፀጋዬ “ባለፈው ዓመት ቡድኑን በሁለተኛው ዙር ስለተቀላቀልኩ ቡድኔ በጥብቅ የሚከላከል እና በመልሶ ማጥቃት የሚጫወት ነበር። በዚህ ዓመት ግን ኳስ የሚቆጣጠር እና የሚያጠቃ ቡድን ይሆናል። በተለይም ጎል የምናገኝበት መንገድ ከዋናዎቹ አጥቂዎች የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከአማካዮቻችንም ጎሎች እንጠብቃለን። ለዚህም እየሰራን ነው።” ብለዋል።