በኢትዮጵያ ቡና እና በፌዴሬሽኑ መካከል ዛሬ የተካሄደው ውይይት ዕልባት ሳያገኝ በቀጠሮ ተለያይተዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የ2010 የአዲስ አበባ ስታድየም ገቢ ድርሻ እንዲሰጠው እና የዘንድሮው የውድድር ዘመንን የስታድየም ትኬት ሽያጭ በክለቡ አማካኝነት እንዲከናወን፤ ይህ የማይሆን ከሆነ እንደማይጫወቱ በመግለፅ በይፋ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ዙርያ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ቡና ተወካዮችን ለዛሬ ለማነጋገር ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል።
ከ10:00 ጀምሮ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በተካሄደው ውይይት በፌዴሬሽኑ በኩል ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዐወል አብዱራሂም (ኮሎኔል) ፣ ሰውነት ቢሻው፣ የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ ፣ የፋይናስ ክፍል ኃላፊው አቶ ነብዩ እና የማርኬት ክፍል ኃላፊው አቶ ኢሳይያስ ሲገኙ፤ በኢትዮዽያ ቡና በኩል የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ይስማሸዋ ሥዩም፣ አዲሱ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ እና የደጋፊ ማኅበሩ ፕሬዝደንት አቶ ክፍሌ አማረ ሲገኙ የስታድየሙ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነው የስፖርት ኮሚሽን ተወካይም ተገኝተዋል ።
ሦስት ሰዐት በቆየው ውይይት በኢትዮዽያ ቡና በኩል የሁለት ዓመታት የስታድየም ገቢ እንዲከፈል፣ ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ባደረገ መልኩ በራስ አቅም የተመልካች መግቢያ ዋጋን በመወሰን እና የሽያጭ ሂደቱን ሙሉ ለሙሉ በክለቡ ብቻ እንዲመራ በማድረግ እንዲሁም በኢትዮዽያ ቡና የጨዋታ ቀን ሌላ ጨዋታ እንዳይደረብ የሚሉ ዋና ዋና የተባሉ የክለቡ አቋሞች በዝርዝር ተገልፀዋል ።
በፌዴሬሽኑ በኩል በተሰጠው ምላሽ ክለቡ ያቀረበው ጥያቄ እንደ ጥያቄ ተገቢ መሆኑ ተገልጾ አጠቃላይ ያለውን ህግ እና ደንብ በዝርዝር ማየት እንደሚያስፈልግ፣ ጥያቄው የሚያስከትለውን ውጤት በእርጋታ በመመልከት የፌዴሬሽኑን አቋም ይዘው ለመቅረብ ለቀጣዩ ሳምንት ሐሙስ ቀጠሮ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ቡናም በመጀመርያው ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ እሁድ ጥቅምት 18 ከድሬዳዋ ከተማ ጋር እንዲያደርግ ተስማምተው ተለያይተዋል ።