ተመስገን ገብረኪዳን ስላሳካው ታሪክ ፣ በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ስላለመካተቱ…

ተመስገን ገብረኪዳን በተከታታይ ሁለት ዓመታት በተሳተፈባቸው የሀገር ውስጥ ውድድሮች ማሳካት ይጠበቅበት የነበሩትን የዋንጫ ክብሮች በሙሉ ማግኘት ችሏል። በ2009 በከፍተኛ ሊግ ከጅማ ከተማ (ጅማ አባ ጅፋር) ጋር አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። በ2010ም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ቻምፒዮን መሆን የቻለው አጥቂው በክረምቱ የዝውውር መስኮት መከላከያን ተቀላቅሏል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች በወቅቱ ሳይጠናቀቁ ወደ ዘንድሮ በመዞራቸው ተመስገን ተጨማሪ ክብሮችን ከሌላ ክለብ ጋር የማሳካት ዕድል ተፈጥሮለታል። ከመከላከያ ጋር የተሳተፈባቸው የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታዎችም በዋንጫ በመጠናቀቃቸው ሶስቱን ክብሮች ከሁለት ክለቦች ጋር ሆኖ ያሳካ ታሪካዊ ተጫዋች መሆን ችሏል። ተመስገን በስኬቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል ።

የጅማ አባጅፋር የሁለት ዓመት ቆይታህ በብዙ ረገድ በጣም ስኬታማ ነበር። ለቀጣይ የእግርኳስ ህይወትህም ጥሩ መነሻ ነው። አንተ የጅማ አባ ጅፋር ቆይታህን እንዴት ትገልፀዋለህ?

አንተ እንዳልከው ነው ፤ ያለፉትን ዓመታት አቅም እያለኝ ተውጬ ቆይቼ ጅማ አባ ጅፋር በቆየሁባቸው ጊዜያት በእግር ኳስ ዕድገቴ ላይ ብዙ ለውጦች ያመጣሁበት እና በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረኩትን ጊዜ አሳልፊያለው። በተለይ ጅማ አባ ጅፋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ በኃላ የተሰጠኝን የመጫወት ዕድል በሚገባ ተጠቅሜበታለው። አስታውሳለው ከሀዋሳ ከተማ ጋር የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ላይ ነበር ተቀይሬ የገባሁት። አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እምነት ጥሎብኝ ዕድሉን ስለሰጠኝ ባሳየሁት ጥሩ እንቅስቃሴ ዓመቱን ሙሉ በጥሩ አቋም እንድጫወት ረድቶኛል ፤ ትልቅ መሻሻል እንዳሳይም አስተዋፆኦ ነበረው። ከጅማ አባ ጅፋርም ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ ውጤታማ በመሆን የዋንጫው አሸናፊ በመሆናችን በጣም ደስተኛ ነኝ ። ለእኔ በአጠቃላይ ያለፉት ሁለት ዓመታት በጣም ስኬታማ ነበሩ።

ምንም እንኳ ከመከላከያ ጋር በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የመሳተፍ ዕድሉን ብታገኝም ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በቻምፒዮንስ ሊጉ የመጫወት አጋጣሚውን ትተህ ነው ዝውውሩን የፈፀምከው…

ወደ መከላከያ ለማምራት እንደ ምክንያትነት የማስቀምጠው በመጀመርያ የቤተሰብ ጉዳይን ነው። ሁለቱን ዓመታት ከቤተሰብ ርቄ መኖር ከብዶኝ ነበር። ከቤተሰብ ጋር አብሮ ለመሆን ስል ነው ወደ መከላከያ ለመምጣት የወሰንኩት። በመቀጠል አብዛኛው የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች በመልቀቃቸው ምክንያትም ነበር የወሰንኩት። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ብጫወት ደስተኛ ነበርኩ። ነገር ግን ወደ መከላከያ ስመጣ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የመሳተፍ ዕድል እንደማገኝ ራሴን አሳምኜው ስለነበር በመሳካቱ በጣም ደስተኛ ነኝ።

በመከላከያ ከወዲሁ ዋንጫዎችን አንስተሀል። አጀማመርህን እንዴት አየኸው ?

በመከላከያ የእስካሁኑ ቆይታዬ በአብዛኛው ያሰብነውን ማሳካት ችለናል። እንደ ጅማሬ በጣም ጥሩ የሚባል ነገር ነው። እንደ ቡድን ደግሞ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በአብዛኛው የሚያዘጋጀን ኳስን መሰረት ባደረገ ልምምድ ነው። የሜዳ ላይ አጨዋወታችንም በኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በቡድኑ ውስጥ ልምድ ያላቸው እና አዳዲስ ተጫዋቾች ይገኛሉ። ልምድ ያላቸውም በብዙ ነገር እያገዙን ስለሆነ በጣም አሪፍ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው ፤ ከዚህ በኋላም ስኬታማ እንሆናለን ብዬ አስባለው።

ተመስገን አምና ፕሪምየር ሊጉን ከጅማ አባ አባጅፋር ጋር ፣ የኢ ትዮጵያ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ደግሞ ከመከላከያ ጋር በማንሳት ሶስቱን ክብሮች ከሁለት ክለቦች ጋር ሆኖ ያሳካ ታሪካዊ ተጫዋች ሆኗል። ይህን አሳካለው ብለህ አስበህ ታውቃለህ ?

እውነት ለመናገር ይህን ታሪክ አሳካዋለው ብዬ አስቤ አላውቅም። ሆኖም ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ‘እኛ ዛሬ አሸናፊ እንሆናለን አንተም ሦስቱን ዋንጫ አንስተህ ታሪካዊ ተጫዋች ትባላለህ’ በማለት ፍሬው ሰለሞን ሲነግረኝ ‘እኔ ሁለት ጨዋታዎችን በጉዳት ባለመጫወቴ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ስለምሆን አንተ ይህን እንዳሳካ ያለውን ነገር ተወጣ’ ብዬው ነበር። ያኔም ነው ይህ ሀሳብ የመጣልኝ እንጂ ምንም አላሰብኩትምም ፣ አልሰማሁምም። በውጪ ሀገራት ከጨዋታ በፊት እንደነዚህ ላሉ ነገሮች ትኩረት ተሰጥቶ በስፋት ይነገራ። እኛ ሀገር እንደዚህ አይነት ነገር አልተለመደም። ከጨዋታው በኋላ ታሪክ መስራቴንም ያሳወቀው ሶከር ኢትዮጵያ ብቻ ነው። በመሆኑም ታሪክ በመስራቴ ብዙም ደስተኛ አልሆንኩም ፤ የተሰማኝም ስሜት የለም። እናንተ ብቻ ናችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ የፃፋችሁት። አስቀድሞ ቢነገር እና በኋላም ሁሉም ሽፋን ቢሰጠው ኖሮ ደስተኛ ልሆን እችል ነበር ።

ያለፉትን ሁለት ዓመታት ወቅታዊ አቋምህ መልካም የሚባል ሆኖ ሳለ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ አልደረሰህም። አንተ ለምን አልተጠራውም ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ ?

የተጫዋች የመጨረሻው ግቡ በክለብ ቀጥሎም በብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ውጪ መጫወት ነው። ለጅማ አባ ጅፋር ቻምፒዮን መሆን ትልቁ ስኬት የፊት አጥቂዎቹ ነበርን። አንዱ የውጪ ተጫዋች ሲሆን የቀረውት ደግሞ እኔ ስለነበርኩ ለብሔራዊ ቡድን ቅድሚያ ይሰጠኝ ይሆናል ብዬ ብጠብቅም ለሙከራ እንኳን ሳልጠራ ቀርቻለው። እንደዚህም ሆኖ በኢቢሲ የኮከቦች ምርጫ ከ10 እጩዎች ውስጥ መግባት ችያለው። ይህ ለእኔ ግራ አጋብቶኛል። አለመጠራቴ የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም እኔም አልገባኝም። ጠንክሬ ሰርቻለው ፣ ስኬታማም ሆኛለው። አሁንም ጠንክሬ እሰራለው። አለመጠራቴ ምንም ሞራሌንም ሆነ አቅሜን ዝቅ አያደርገውም ፤ እንዲያውም ብርታት ነው የሚሆነኝ። በእግር ኳስ ወቅታዊ ብቃት አስፈላጊ ነው። ከዓምናው የተሻለ ነገር ከመከላከያ ጋር ሰርቼ ምን አልባት በብሔራዊ ቡድን ያልተጠራሁበት ድክመት ምንድን ነው ብዬ ያሰብኩትን አሟልቼ ለመጠራት ጠንክሬ እሰራለው።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ