የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሜቴ በያዝነው 2011 የውድድር ዓመት ላይ የሚተገበሩ የተሻሻሉ የጨዋታ ህጎችን የሚመለከት ሰልጠና ለፕሪምየር ሊግ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች ከጥቅምት 13-15 ሰጥቷል።
ለሶስት ተከታታይ ቀናት በቆየው ስልጠና ላይ 127 ዳኞች እና 43 የጨዋታ ታዛቢዎች (ኮሚሸነሮች) ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በህግ እና የአካል ብቃት ኢንስትራክተሮች አማካኝነት በክፍል ውስጥ በቃል፣ በቪድዮ እንዲሁም በተግባር በሜዳ ላይ ትምህርት ተሰጥቷል።
በትላንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ሆቴል ከሰዓት ላይ በነበረው የስልጠና ማጠቃለያ ላይ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ዐወል አብዱራሂም (ኮ/ል) እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በስፍራው ተገኝተው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። ከኮሚሽነሮች በኩል ስልጠናው በመዘጋጀቱ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ሊፈቱ ስለሚገቡ ችግሮች ሀሳብ ተሰጥቷል። የዳኞች እና ኮሚሽነር ቅጣት ግልፅ መሆን አለበት፣ ጣልቃ ገብነት መቅረት አለበት፣ ብቃት ያላቸው ሴቶች ዳኞቻችን ፕሪምየር ሊግ እንዲዳኙ ይደረግ፣ የዳኞች ኮሚቴ ውስጥ ሴቶች ቢካተቱ፣ ፌዴሬሽኑ ከክልል ፌዴሬሽኖች ጋር መደበኛ ግንኙነት ይመስርት፣ ዳኞች ከኮሚሽነሮች ጋር ጤናማ ግንኙንት ይኑራቸው፣ የክፍያ መጠን የሚሻሻልበት መንገድ ይፈለግ፣ ፌዴሬሽኑም ሆነ የዳኞች ኮሜቴ በህግ እና በድንቡ መሰረት ይመሩ በሚሉ ሀሳቦች ላይ ያተኮሩ አስተያየቶች ቀርበዋል።
ስልጠናው ላይ የተሳተፉት ዳኞች በበኩላቸው በስልጠናው ደስተኛ እንደሆኑ እና የተሻለ ትምህርት እንዳገኙበት ገልፀው ኢንስትራክተሮቹንም አመስግነዋል። ዳኞች ራሳቸውን ማስከበር አለባቸው፣ ምደባ ላይ ያለው አለመጣጠን ሊቀረፍ ይገባል፣ የዳኞች ደረጃ ሊወጣላቸው ይገባል፣ የዘር እንዲሁም የብሔር ክፍፍሉ ሊወገድ ይገባል፣ በ2010 በዳኞች ማኅበር አማካኝነት የተጠየቁ 10 ጥያቄዎች መልስ ይሰጣቸው፣ የዳኞች የክፍያ ጉዳይ በድጋሚ በአፅንኦት ይታይ የሚሉ ጥያቄዎችም አቅርበዋል።
ከዳኞች እና ኮሚሽነሮች ሀሳብ እና ጥያቄ ከተስተናገደ በኋላ በፌዴሬሽኑ በኩል ምላሸየሰጡት ም/ል ፕሬዝዳንቱ ኮ/ል ዐወል “በዚህ አራት ዓመታት ውስጥ ለውጥ ማምጣት አለብን ብለን ነው የተነሳነው። እግር ኳሳችን ልማት ይፈልጋል፤ ከልማቱ አንዱ የሆነው የዳኞች እና የኮሚሽነሮችን አቅም ከፍ የማድረግ ጉዳይ ነው። ለእግርኳሱ ልማት ታስፈልጉናላችሁ፤ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ልዩ አምባሳደር ናቹየችሁ። ቤቱ ካነሳው ሀሳብ ውስጥ የሴቱችን ጉዳይ የምንቀበለው እና በቀጣይ በሚቋቋሙ ኮሜቴዎች ውስጥ በማሳተፍ ስራ የምንጀምር ይሆናል። ማንኛውም ዳኛ በአካል ወደ ፌዴሬሽኑ በሚመጣበት ወቅት በተቻለን መንገድ ቶሎ እንዲስተናገድ ድልድይ ዘርገተናል። የአበል እና የክፍያ ጉዳይ በቀጣይ እናስተካክላለን። በማንኛውም ጨዋታ በቂ ኃይል እንደሚመደብላችሁ ቃል እንገባለን። የ2011 ውድድር ዓመት የሰላም የፍቅር ይሁንልን።” በማለት የተነሱትን ሀሳቦች እንደ ጥሩ ግብዓት እንደሚወስዷቸው አክለው ገልፀዋል።
በቀጣይ የዳኞች ኮሜቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር ቤቱ ያነሳውን ጥያቄ እና አስተያየት እንደተቀበሉ በመግለፅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሜቴ በያዝነው ዓመት ስራውን በአዲስ መልክ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቱን መጨረሱንና በርካታ ስራዎችን ለመስራት እንዳሰቡ ተናግረዋል። ከዳኞች ሆነ ከኮሚሽነሮች የሚፈለገው ነገር ቢኖር ግልፀኝነት፣ ፍቅር እና ለሙያው ታማኝነት መሆኑንም ገልፀዋል። አቶ ዮሴፍ አክለውም የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ዋንኛው አላማው የዳኞች፣ የኮሚሸነሮች እና የኢንስትራክተሮችን ስራ በማቀላጠፍ ውድድሮችን በሰላም እንዲጠናቀቁ ለዚህም የፊፋ የጨዋታ ህግና የኢትዮጽያ እግርኳስ ፌዴሪሽን የውድድር ደንብ መሰረት በማድረግ ለተወዳዳሪ ቡድኖች ፍትሀዊ ውሳኔ በመስጠት ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የውድድር ሂደት በመፍጠር ብቃት ያላቸው ዳኞች ኮሚሽነሮች መፍጠር መሆኑን ገልፀዋል።
ኮሚቴው በዚህ ዓመት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የዳኞችን የአካል ብቃት ዝግጅት በኢንስትራክተሮችና በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በጋራ የልምምድ እና የግምገማ ሂደት ማዘጋጀት፣ የዳኞች የእግር ኳስ ህግ እውቀትን የአቅም ግንባታና ማሻሻያ ኮርሶች በመስጠት ማብቃት፣ በሜዳ ላይ የሚሰጡ የህግ ውሳኔዎችን ወጥነት እንዲኖረው ማድረግ፣ ዳኞች በዳኝነት ብቃታቸው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀጥሎም በዓለም ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ማድረግ፣ የዳኞች የግለ ማኅደር (ፕሮፋይል) በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት፣ የዳኞች ምድባ በጥራት እና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ መስራት እንደሆነ የገለፁት አቶ ዮሴፍ በመጨረሻም ማንኛውንም የዳኝነት፣ የታዛቢነትም ሆነ የኢንስትራክተርነት እና ሌሎች ጥያቄዎች ለማቅረብ ሲፈልጉ ጉዳያቸውን በጽ/ቤት በኩል በማሳወቅ ከሚደረጉ ግንኙነቶች በስተቀር በተናጠል ከኮሜቴው አባላት ጋር ግንኙነት ማድረግ የማይቻል መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል።
በስተመጨረሻም ስብሰባው በቀጣይ እርከን ላይ ባሉ ዳኞች የሚቀጥል መሆኑ ተገልፆ የ2011 የውድድር ዓመት መልካም ውድድር እንዲሆን በመመኘት የብሔራዊ ዳኞች ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በስብሰባው ላይ ከተገኙት አባላት ጋር ሰለምታ በመለዋወጥ ትውውቅ አድርገዋል።
ማስታወቂያ |
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ |