አስተያየት ፡ ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ አሰልጣኝ ሥዩምን ውጤታማ አድርጎታል

አስተያየት በዘርዓይ ኢያሱ

የአንድ አሰልጣኝ ጥሩነት መለኪያዎች ከሚባሉት መካከል አንዱ ጨዋታ አንብቦ ውጤት መቀየር የሚችል ውሳኔ መስጠት መቻሉ ነው፡፡ በሃገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ይህንን ያደረጉ አሰልጣኞችን እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የጨዋታውን እንቅስቃሴ እየቃኘ የወሰዳቸው ውሳኔዎች በመጨረሻ ቡድኑን ሻምፒዮን ማድረጋቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

4-4-2 ዳይመንድ

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጨዋታውን የጀመረው በ4-4-2 ዳይመንድ ነበር፡፡ ይህ ፎርሜሽን በኳስ ቁጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚስችል በመሆኑ በማራኪ ጨዋታ የታጀበ ድል ማግኘት የአሰልጣኙ ፍላጎት እንደነበር ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ነገር ግን አማካዩ ቴዎድሮስ ታፈሠ 26ኛው ደቂቃ ላይ በቀጥታ በቀይ ካርድ መውጣጡን ተከትሎ የጨዋታ እቅዱን ሊቀይር ተገዷል፡፡ ከቀይ ካርዱ በኋላ አጥቂውን ፍፁም ገብረማርያምን አስወጥቶ የአማካይ ተከላካዩ በኃይሉ ግርማ ተክቶቷል፡፡

ይህ በመሆኑ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የጨዋታውን ፎርሜሽን ወደ 4-4-1 ቀይሯል፡፡ ይህ ውሳኔ በወቅቱ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ አሰልጣኙ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የቴዎድሮስ ታፈሠ በቀይ ካርድ መውጣት በተጋጣሚው የቁጥር ብልጫ እንዲወሰደበት ስለሚያደርግ የመከላካሉን ሚዛን ለመጠበቅ በአራት ተከላካይና በአራት አማካይ መጫወት ነበረበት፡፡

ይህንን በማድረጉ ተጨማሪ ጎሎች እንዳይቆጠርበት ከማድረጉ ባሻገር ጎል አስቆጥሮ 1ለ1 መሆን በመቻሉ ውሳኔው አዋጪ መሆኑን ተመልክተናል፡፡

3-4-2 አቻነቱን ያስጠበቀ ለውጥ

መከላከያ አንድ ተጨዋች በቀይ ካርድ ሲወጣበት ከጅማ አባ ጅፋር በኩል ይጠበቅ የነበረው ውሳኔ በአራት ተከላካይ መጫወቱን ትቶ በሶስት ተከላካዮች መጫወት ነበር፡፡ ይህ ማለት አንድ ተከላካይ ቀንሶ አማካይ በመጨመር 4-3-3 የነበረውን ፎርሜሽን ወደ 3-5-2 መቀየር አልያም አንድ ተከላካይ ቀንሶ አጥቂ በመጨመር ወደ 3-4-3 በመቀየር በይበልጥ የማጥቃት ኃይሉን መጨመር ይቻል ነበር፡፡

ነገር ግን ጅማ አባ ጅፋሮች ለአንድ አጥቂ (ለምንይሉ ወንድሙ) አራት ተከላካዮችን በመጠቀማቸው የቁጥር ብልጫውን መጠቀም ሳይችሉ በመቅረታቸው ዋንጫን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በእለቱ ታክቲክን በመለዋወጥ ከተጋጣሚ አሰልጣኞች ብልጫ የነበረው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጅማ አባ ጅፋር በአራት ተከላካይ የመጫወት እቅዱን እንደማይቀይር በመረዳቱ ይመስለኛል 75 ተኛው ደቂቃ ላይ ድፈርት የተሞላበት ነገር ግን ውጤታማ ያደረገውን ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ውሳኔው የግራ መስመር ተከላካዩን አለምነህ ግርማ በአጥቂው ተመስገን ገብረኪዳን መተካት ሲሆን 4-4-1 ቅርፅ የነበረው ፎርሜሽን ወደ 3-4-2 ቀየረ፡፡ ከዚህ የምንረዳው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የአጥቂ ቁጥር ጨምሮ አጥቅቶ መጫወት መፈለጉ ነው፡፡ ከዚህ ለውጥ በኋላ መከላከያ ይበልጥ ጉልበት አግኝቶ ተደጋጋሚ የጎል እድሎችን መፍጠር ችሏል፡፡

በዚህ ግዜ ምንም እንኳን መከላከያ ተጨማሪ ጎል ማግባት ባይችልም ቢያንስ ቢያስ ጨዋታውን ወደ መለያ ምት በማድረስ የአንድ ተጨዋች በቀይ ካርድ መውጣት ተፅኖ ወደ ማይፈጥርበት መለያ ምት ደርሷል፡፡ በመጨረሻም 4ለ2 አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል፡፡

የጅማ አባ ጅፋር ክፍተቶች

ጅማ አባ ጅፋር በ2010 ዓ.ም ቡድኑን ሻምፒዮን ያረጉትን አብዛኛዎቹን ተጨዋቾች እንደማጣቱ መልሶ ግንባታ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው፡፡ የተደራጀ ቡድን ይዞ ለመቅረብ ግዜ የሚፈልግ ቡድን መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫና በአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ተመልክተናል፡፡

ነገር ግን ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ ከታክቲክ ጋር ተያያዠነት ያላቸው ክፍተቶች ቡድኑን ዋጋ እንዳስከፈሉት መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ ታፈሰ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ በአራት ተከላካይ ለመጫወት መወሰናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አራት ተከላካዮች እስከመጨረሻው ደቂቃ ከመጠቀም ይልቅ ተከላካይ ቀንሶ አጥቂ ወይም አማካይ በማስገባ የማጥቃት የበላይነቱን መውሰድ ይቻል ነበር፡፡

ነገር ግን ይህን ባለመደረጉ መከላከያ የልብ ልብ እንዲሰማው አድጓል ባይ ነኝ፡፡ ሌላኛው ክፍተት ከተጨዋች አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ 36ኛው ደቂቃ ላይ የአማካይ ተከላካዩ አክሊሉ ዋለለኝ ወጥቶ አጥቂው ዲዲየር ሊብሬ ገብቷል፡፡ የአክሊሉን ቦታ እንዲተካ የተደረገው ደግሞ ወደ ማጥቃቱ አዘንብሎ ሲጫወት የነበረው ሄኖክ ግምቴሳ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የአክሊሉ መውጣት የቡድኑን የማጥቃና የመከላከል ሚዛን አሳጥቶታል፡፡ ይህንንም አሰልጣኞቹ የተረዱ ይመስላል ከአክሊሉ ጋር ተመሳሳይ የጨዋታ ባህሪ ያለውን ንጋቱ ገብረሥላሴን በሁለተኛው ግማሽ በኤልያስ ማሞ ተክቷል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ጅማ አባ ጅፋር የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ዋንጫውን አጥቷል፡፡

አክሊሉ ዋለልኝ ቢቆይስ?

አክሊሉ 36ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ሲወጣ ብዙዎቻችን የመሠለን በጉዳት መውጣቱን ነው፡፡ ነገር ግን አልነበረም፡፡ አክሊሉ ለተከላካዮች በቂ ከለላ መስጠት የሚችል እንደመሆኑ መጠን ሜዳ ውስጥ ቢቆይ የመከላከል ሚዛኑን መጠበቅ ይቻላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ግዜ በሶስት ተከላካይ ቢጫወት እንኳን የመከላከል ስጋት አይኖርበትም፡፡ ይህ ባለመደረጉ የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተገድቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የመከላከያ ተጨዋቾች በጅማ አባ ጅፋር የሜዳ ክፍል ያለ ጫና ኳስ እንዲቀባበሉ ረድቷቸዋል፡፡ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችለው አክሊሉ አልያም እንደ እሱ ያሉ ተጨዋቾች እንደመሆናቸው የቡድኑ የመከላከልና የማጥቃት ሚዛን ባልተፋለሰ ነበር፡፡

ዳንኤል አጄይ እና ኤርሚያስ ኃይሉ

በመጀመሪያው ግማሽ አልፎ አልፎ ካስተዋልናቸው ክስተቶች መካከል አንዱ በግብ ጠባቂው በዳንኤል አጄይ እና በአጥቂው ኤርሚያስ ኃይሉ መካከል የነበረውን ግንኙነት ነው፡፡ ሁለቱ ተጨዋቾች ሊያገናኝ የቻለው ብቸኛ ነገር ቢኖር የዳኤል ኦጄ ረጅም ኳሶች ናቸው፡፡ የዳንኤል ረጅም ኳሶች የኤርሚያስን ፍጥነት ለመጠቀም የታሰበ ቢሆንም ተጨዋቹ ያለበትን ሁኔታ ያላገነዘበ በመሆኑ በዚህም ውጤታማ መሆን አልተቻለም፡፡ ኤርሚያስ ፈጣን ተጨዋች ቢሆንም የአየር ላይ ኳሶችን ከተጋጣሚዎቹ ማሸነፍ የሚችል ባለመሆኑ ረጃጅም ኳሶችን ለሱ ደጋግሞ መጣሉ አግባብ አልነበረውም፡፡

ግን ደግሞ ሁሌም ለኤርሚያስ ረጅም ኳሶችን መጣል አያዋጣም ማለት አይደለም፡፡ ወደ መሃልኛው የሜዳ ክፍል ተጠግቶ የሚከላከል ቡድን ሲያጋጥም ከተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍት ቦታ በፍጥነቱ መጠቀም ይችላል፡፡ በተረፈ ግን የጋራ ኳሶችን ለኤልያስ ረጃጅም ኳሶችን መጣል አወጪ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የመከላከያ የመሃል ተከላካዮች አበበ ጥላሁንና አዲሱ ተስፋዬ ከግብ ጠባቂው ጋር የነበራቸውን ርቀት ጠብቀው ይጫወቱ ነበርና፡፡

ማጠቃለያ

ሁለቱ ቡድኖች በአፍሪካ መድረክ ሃገራችንን ወክለው የሚሳተፉ እንደመሆናቸው መጠን ረጅም ርቀት እንዲጓዙ እንፈልጋለን፡፡ ስለሆነም ጠንካራ ጎናቸው እንዳለ ሆኖ በድክመቶቻቸው ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ ከታክቲክ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ከሰሞኑ ጨዋታዎች ተመልክተናል፡፡ ይህንንም ለማረም የሃገር ውስጥ ውድድሮችን በአግባቡ መጠቀም ለአህጉራዊው ውድድር የሚሆኑ ግብአቶችን ለማግኘት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡


በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጋር የተያያዙ አስተያየት አዘል ጽሁፎችን ድረ-ገጻችን ላይ እንደምናስተናግድ እየገለጽን በኢሜይል አድራሻችን abgmariam21@gmail.com ልታጋሩን ትችላላችሁ፡፡