የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምክክር መድረክ አዘጋጀ

አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከአዲስ አበባ መስተዳድር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የፕሪምየር ሊግ፣ የከፍተኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግ ክለቦች እና ደጋፊዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት የምክክር መድረክ አዘጋጀ።

ነሐሴ 2010 በጎደሉት የስራ አስፈፃሚ አባላት ምትክ ተጨማሪ ስራ አስፈፃሚዎችን እና አዲስ ፕሬዝደንት የመረጠው የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን 13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን በስኬት ባጠናቀቀበት ማግስት በስሩ ከሚገኙት የፕሪምየር ሊግ ፣ የከፍተኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግ ፣ የከፍተኛ እና አንደኛ ዲቪዚዮን ቡድኖች ፣ ደጋፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ማክሰኞ ጥቅምት 20 ከ07:30 ጀምሮ በኢንተር ኮንትኔታል አዲስ ሆቴል የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

የምክክር ጉባኤው የተዘጋጀበት አላማን የሚናገሩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሐ (ኢንጂነር) “የምክክር መድረኩ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ክለቦች እና በፌዴሬሽኑ መካከል ያለውን ግኑኝነት ማጠናከር እና ፌዴሬሽኑ ለክለቦቹ ማድረግ ስለሚገባው እገዛ እንዲሁም የአዲስ አበባን እግርኳስ ለማሳደግ በታዳጊዎች ላይ መሰራት ስለሚገባ ጉዳይ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተርያ ዙርያ ችግሮችን ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት በሚሉ እና መሰል ጉዳዮች ዙርያ ከተሳታፊዎቹ ጋር ጥልቅ ውይይት ለማድግ የተዘጋጀ ጉባኤ ነው። በምክክር መድረኩ ለእግርኳሱ እድገት ጠቃሚ ሀሳብ ያነሳሉ የተባሉ ከ700 ባላይ ተሳታፊዎች የጠራን ሲሆን በተለይ የከተማችን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኩማ (ኢንጂነር) ይገኛሉ” ብለዋል።

ዓመት ጠብቆ የአዲስ አበባን ከተማ ዋንጫን ከማዘጋጀት ውጭ ለአዲስ አበባ እግርኳስ እድገት ብዙም ውጤታማ ስራ አልሰራም ተብሎ ወቀሳ የሚቀርብበት ፌዴሬሽኑ እንደነዚህ ያሉ የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀቱ በቀጣይ እየተዳከመ የመጣውን የአዲስ አበባ እግርኳስን እንዲያንሰራራ ለማድረግ እንደ በጎ ጅምር ተደርጎ ይወሰዳል።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ