የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | ባህር ዳር ከተማ

ነገ በሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ያሳለፉትን የዝግጅት ጊዜ የሚያስቃኘው መሰናዷችን ባህር ዳር ከተማ ላይ ደርሷል።

በ2011 የውድድር ዓመት ወደ ሊጉ ብቅ ካሉ ክለቦች መካከል ባህር ዳር ከተማ አንዱ ነው። የከፍተኛው ሊግ ምድብ ‘ሀ’ን በአንደኝነት ያጠናቀቀው ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደግ ፍንጭ ያሳየው ቀደም ብሎ ነበር። የውድድሩ የመጀመሪያ ዙር ማብቂያ ላይ የተቆናጠጠውን አንደኝነት ይዞ እስከ ውድድሩ መጠናቀቂያ ዘልቋል። በ27ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ መድንን 2-1 የረታበት ጨዋታም ባህር ዳር ወደ መጀመሪያው የሊግ እርከን ማደጉ የተረጋገጠበት ሆኗል። ሆኖም ነሀሴ 29 በአዳማ የተደረገው እና የሁለቱን ምድቦች አሸናፊ ባገናኘው የፍፃሜ ጨዋታ በደቡብ ፖሊስ 1 0 ተሸንፎ የከፍተኛ ሊጉ ቻምፒዮን የመሆን አጋጣሚው አልፎታል። ያም ቢሆን በቅርብ ዓመታት ወደ ሊጉ የሚመጡ ክለቦች የሚያሳዩት አቋም ባህር ዳርም ጥሩ ጉዞ ሊያደርግ የሚችልበት ሰፊ ዕድል እንዳለ የሚያመላክት ነው።

እስከ አዲሱ ዓመት መግቢያ ድረስ በውድድር ውስጥ የቆዩት ባህር ዳሮች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካሳደጋቸው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር ለመቀጠል በመወሰን ውላቸውን አራዝመዋል። በብዛት እንደሚታየው ከከፍተኛ ሊግ የሚመጡ ክለቦች ከነባር ተጫዋቾቻቸው ጋር የመቀጠል ዕድላቸው ጠባብ ነው። በባህርዳር በኩል እንደ አዲስ ከተፈፀሙት ዝውውሮች ባለፈ ከቡድኑ ጋር የሚቀሩ አስራ ሁለት ተጫዋቾችንም በመያዝ ሊጉን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል። በዚህም መሰረት ወሰኑ ዓሊ ፣ ምንተስኖት አሎ ፣ ሳለዓምላክ ተገኝ ፣ ኄኖክ አቻምየለህን ፣ ዳግም ሙሉጌታ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ፣ ደረጄ መንግስቱ ፣ ፍቃዱ ወርቁ ፣ ግርማ ዲሳሳ፣ ተስፋሁን ሸጋው ፣ ወንድሜነህ ደረጄ እንዲሁም አቤል ውዱ በታችኛው ሊግ ከጣና ሞገዶቹ ጋር የነበራቸውን ጊዜ ለማራዘም እስካሁን ውል ያደሱ ተጫዋቾች ናቸው።

ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ በተለያዩ ክለቦች በመጫወት ባሳለፉ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ባደረገበት የዝውውር ተሳትፎም አስር ተጫውቾችን አስፈረሟል፡፡ ሀሪስተን ሄሱ (ግብ ጠባቂ ከኢትዮጵያ ቡና) ፣ ጃኮ አራፋት (መሀል አጥቂ ከወላይታ ድቻ) ፣ አሌክስ አሙዙ (ተከላካይ ከአርባምንጭ ከተማ) ፣ አስናቀ ሞገስ (መስመር ተከላካይ ከኢትዮጵያ ቡና) ፣ ማራኪ ወርቁ (የመስመር አጥቂ ከመከላከያ) ፣ እንዳለ ደባልቄ (የመስመር አጥቂ ከጅማ አባጅፋር) ፣ አብርሃም ታምራት (ተከላካይ ከኢትዮጵያ መድን) ፣ ኤልያስ አህመድ (አማካይ ከሰበታ ከተማ) ፣ ታዲዮስ ወልዴ (አማካይ ከወላይታ ድቻ) እና አህመድ ዋካራ (አይቮሪኮስታዊ አጥቂ) አዳዲሶቹ የባህር ዳር ተጫዋቾች ናቸው። ” በየመጫወቻ ቦታው ላይ ያመጣናቸው ተጫዋቾች አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እንደተመለከትነው ዉጤታማ ነበሩ። ነባሮችም አንደዚሁ በጣም ጥሩ ነበሩ። ስለዚህ ያለዉ ዉህደት ከዕለት ወደ ዕለት በጣም መሻሻል እያሳየኝ ነው እና በዝውውሮቹ በጣም ደስተኛ ነኝ። ” የሚሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ናትናኤል በልቲ እና ኃይለየሱስ ደረሰ የተባሉ ወጣት ተጫዋቾችንም በቡድናቸው እንዳካተቱ ጠቁመዋል።

ዘግየት ብሎ መስከረም ዘጠኝ ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በባህር ዳር የጀመረው ክለቡ በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቦለት ሳይመጣ የቀረው የናይጄሪያው ኳራ ዩናይትድን ተክቶ በመጨረሻ ሰዓት በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ መጥቷል። በተሳትፎውም መልካም እንቅስቃሴን በማድረግ እስከ ፍፃሜው ዘልቆ በኢትዮጵያ ቡና በመሸነፍ በሁለተኝነት አጠናቋል። ” በነበረን የዝግጅት ጊዜ በጣም ደስተኛ ነኝ። በተጫዋቾቼም ደስተኛ ነኝ። ሁሉንም ነገር እንዳሰብነው ለመድረግ ትግል እያደረግን እንገኛለን። እንግዲህ በፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በጥሩ ተፎካካሪነት እና በጥሩ ስነምግባር ዓመቱ መጨረሻ ላይ መልካም ውጤት እናስመዘግባለን የሚል አመለካከት አለኝ።” የሚሉት አሰልጣኝ ጳውሎስም ጌታቸው በአዲስ አበባ ዋንጫ ያደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ተጫዋቾቻቸውን ለመመዘን እንደጠቀማቸው አልሸሸጉም።

ባህርዳር በመጀመሪያው የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው የሚኖረውን የጨዋታ ዘይቤ ተጠይቀው መልስ የሰጡት አሰልጣኙ ” እንደሚታወቀው የምንከተለው አጥቅቶ የመጫወትን ዘዴ ነው። አሁንም ቡድናችንን በዛ መልክ እየገነባን ነው። በsmall sided game (በጠባብ ሜዳ ላይ በውስን ተጫዋቾች መካከል የሚደረግ ጨዋታ) ላይ እና በተለያዩ ቡድን በሚገነቡ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ያለነው። የእስካሁኑ አካሄዳችንም ውጤታማ አድርጎናል ብዬ እገምታለሁ። አዲስ አበባ ዋንጫ ላይም የዚህን ነፅብራቅ ማየት እንደቻን ነው የማምነው። ስለዚህም በዚሁ መልኩ የምንቀጥል ይሆናል። ከፕሪምየር ሊግ አንፃርም በሊጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች መጥተዋል ከነባሮች ጋር በማዋሀድ የተሻለ ነገር እንሰራለን የሚል ዕምነት አለኝ። ” ብለዋል። በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ እንደተመለከትነውም ቡድኑ በዋነኝነት የመስመር አጥቂዎቹን በመጠቀም ጥቃቶችን የመሰንዘር አዝማሚያ ሲያሳይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ደግሞ የጥቃት ምንጮቹ ናቸው።

ክለቦች ለሊጉ አዲስ ሆነው በሚመጡበት ወቅት በተለይም ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ አጨዋወትን መተግበርን ምርጫቸው ያደርጋሉ። በመጨረሻ ግብም ደረጃ የሚያስቀምጡት በሊጉ መቆየትን ነው። የአሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው አስተያየት ግን ቡድኑ ከዚህ በተለየ መንገድ ለመጓዝ ዕቅድ እንዳለው የሚያሳይ ነው። ” እንግዲህ በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችን ውጪ ጥሩ አጨዋወትን ተግብረን እና ጥሩ ነጥብ ሰብስበን ተፎካካሪ ሆነን በፕሪምየር ሊጉ ክስተት እንሆናለን የሚል እምነት አለኝ። ግባችን ለዋንጫ ነው። ሌላ ነገር የለውም። ጠንክረን እንጫወታለን ከየትኛውም ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች የማያንስ ስራ ሰርተናል። ያሉን ተጫዋቾችም በጥራት ከማንም የማያንሱ ፣ ችሎታ ያላቸው እና ሮጠው ያልጠገቡ ስለሆኑ ውጤታማ ሆነን እንጨርሳለን ብዬ እገምታለሁ። ”

ባህር ዳር ከተማ የመጀመሪያ የሊ.ግ ጨዋታውን ጥቅምት 25 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ