ፌዴሬሽኑ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ያለ ፍቃድ በቀጥታ እንዳይተላለፉ አስጠነቀቀ

የኢትዮጵያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍን አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ መተዳደርያ ደንብን መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለክለቦች በላከው ደብዳቤ አሳሰበ።

በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረ 21ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን ሊጀመር ዋዜማ ላይ በምንገኝበት ወቅት ሚዲያዎች ጨዋታዎችን ከፌዴሬሽኑ ፈቃድ ውጭ ማስተላለፍ እንደማይቻል በደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ፌዴሬሽኑ ከ2010 ጀምሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ የማይቻል መሆኑን ከዚህ ቀደም መግለፁን አስታውሶ በደብዳቤው “በ2011 ማንኛውም ውድድር በሚከናወንበት ወቅት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መተዳደርያ ደንብ አንቀፅ 51 መሠረት ፈቃድ ያላገኘ ተቋም ማስተላለፍ የማይችል መሆኑን በጥብቅ እያሳወቅን ደንቡን የማስከበር ኃላፊነት የሁሉም ባለድርሻ አካል መሆኑን በቅድሚያ እናሳውቃለን” ብሏል።

የደብዳቤ ዝርዝር ፍሬ ኃሳብ አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረሦላሴ በሰጡት አስተያየት ህዝቡ መረጃ ማግኘት እንዳለበት ፌዴሬሽኑ ቢያምንም የውድድሩን የሚመራው ፌዴሬሽኑ በመሆኑ በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፈው መገናኛ ብዙሀን ከስፖንሰር ከሚያገኘው ገቢ ፌዴሬሽኑ ተጠቃሚ መሆን ስለሚገባው ውድድሮችን ለማስተላለፍ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ከፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋገር ፈቃድ ሲያገኝ ማስተላለፍ እንደሚችል ገልፀዋል።

ግልፅ የሆነ የብሮድካስቲንግ ህግ እና የፍቃድ መስፈርቶች በሌሉት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከላይ ከተጠቀሰው ደንብ በተቃራኒው በ2010 የውድድር ዓመት በርካታ ጨዋታዎች የቴሌቪዥን እና ራዲዮ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ማግኘታቸው የሚታወስ ነው።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ