ዛሬ ሀዋሳ ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገም በአራት ከተሞች መካሄዱን ይቀጥላል።
አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር |
አዳማ ከተማ በመጀመሪያ ጨዋታው የሊጉን ቻምፒዮኖች ያስተናግዳል። አምና በመጨረሻው ሳምንት ጅማ ላይ ተገናኝተው የነበሩት ሁለቱ ክለቦች በአዳዲስ አሰልጣኞች እየተመሩ ነው ነገ የሚፋለሙት። አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀምን የቀጠረው አዳማ ከተማ ከቁልፍ ተጫዋቾቹ መካከል ሱራፌል ዳኛቸው እና ሙጂብ ቃሲምን አጥቶ በከፍተኛ ሊግ ላይ ያመዘኑ አስራ ሁለት ዝውውሮችን ፈፅሟል። በመሆኑም ከአምናው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቡድን ይዞ ሊጉን እንደሚጀምር ይጠበቃል። በተቃራኒው ጅማ አባ ጅፋር በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ አራቱን ብቻ ያስቀረው የዝውውር መስኮት ላይ አስራ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አካቶ ቅጣት ላይ በሚገኙት አሰልጣኝ ዘማርያም የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። በከንዓን ማርክነህ እና ኤልያስ ማሞ የሚመሩ የአማካይ ክፍሎች ያሏቸው ሁለቱ ቡድኖች ብርቱ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ የሚጠበቃቸው ሲሆን እንደ በረከት ደስታ እና ዲዲዬ ለብሪ ዓይነት አጥቂዎችም የቡድኖቹ የመስመር ጥቃት ጥንካሬዎች እንደሚሆኑ ይገመታል።
አዳማ ከተማ ሙሉ ስብስቡ በመልካም ጤንነት ላይ ሲገኝ የጅማ አባ ጅፋሩ አዲስ ፈራሚ ቢስማርክ አፒያ አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ካስተናገደው ጉዳት አላገገመም።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– አዳማ በ2010 ወደ ሊጉ ያደገው አባ ጅፋርን ያስተናገደበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቀ የሁለተኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በባለሜዳው አባ ጅፋር 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
– የ30ኛ ሳምንቱ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የሊጉን አሸናፊ የለየ እና አዳማ በ2005 ካስተናገደው የመኪና አደጋ በኋላ ባደረገው ጨዋታ ከገጠመው ሽንፈት ቀጥሎ ትልቁን ሽንፈቱ ሆኗል።
ዳኛ
– ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ሮበርት ኦዶንካራ
ሱራፌል ዳንኤል – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱሌይማን መሀመድ
ኢስማኤል ሳንጋሪ – አዲስ ህንፃ
ቡልቻ ሹራ – ከንዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ
ዳዋ ሆቴሳ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ዳንኤል አጃዬ
ዐወት ገብረሚካኤል- ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ
ይሁን እንዳሻው – ኄኖክ ገምቴሳ – ኤልያስ ማሞ
ኤርሚያስ ኃይሉ – ማማዱ ሲዲቤ – ዲዲዬ ለብሪ
ሀዋሳ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ |
የሀዋሳ ባለ ሰው ሰራሽ ሜዳ ስታድየም ሁለተኛ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን ነገ 09፡00 ላይ ያስተናግዳል። ተጋጣሚዎቹ ደግሞ የሜዳው ባለቤት ሀዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ናቸው። ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር የተለያየው ሀዋሳ አሰልጣኝ ኤዲሴ ካሳን የሾመ ሲሆን ለየት ባለ መልኩ አራት ዝውውሮችን ብቻ ፈፅሞ በአብዛኛው ባለፉት ዓመታት ባሳደጋቸው ተጫዋቾቹ ላይ እምነት ጥሎ መቀጠልን መርጧል። የነገ ተጋጣሚው ወልዋሎ ደግሞ በተቃራኒው አሰልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ሲያቆይ እንደ አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች በርካታ ዝውውሮችን መፈፀምን መርጧል። የነገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም በአጫጭር ቅብብሎች ላይ የተመሰረተ ፉክክርን እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል።
ሀዋሳ ከተማ ሙሉ ስብስቡን ይዞ ለጨዋታው ሲቀርብ በወልዋሎ በኩል አዲሱ ግብ ጠባቂ አብዱላዚዝ ኬይታ ፣ አብዱርሀማን ፉሰይኒ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በጉዳት ኤፍሬም አሻሞ በደደቢት ሳለ በተመለከተው ቀይ ካርድ እንየው ካሳሁን ደግሞ በአምስት ቢጫ ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– የአምናው የመጀመሪያ ዓመት የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት አንድ ግብ ብቻ የተቆጠረበት ነበር። ዓዲግራት ላይ ወልዋሎ በፕሪንስ ብቸኛ ጎል ሲያሸንፍ የሀዋሳው ጨዋታቸው ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።
ዳኛ
– ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የሚመራው ፌደራል አሸብር ሰቦቃ ነው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
ሶሆሆ ሜንሳህ
ዳንኤል ደርቤ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ
አዳነ ግርማ – አስጨናቂ ሉቃስ – ታፈሰ ሰለሞን
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – እስራኤል እሸቱ – ቸርነት አወሽ
ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)
ዮሃንስ ሽኩር
ዳንኤል አድሀኖም – ደስታ ደሙ – በረከት ተሰማ – ብርሀኑ ቦጋለ
አማኑኤል ጎበና – አስራት መገርሳ -ዋለልኝ ገብሬ
ሮቤል አስራት – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ዳዊት ፍቃዱ
መቐለ 70 እንደርታ ከ ደደቢት |
ደደቢት መቀመጫውን ወደ መቐለ ካዞረ በኋላ የሚያደርገው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ሆኗል። ሁለቱ ክለቦች በትግራይ ዋንጫ ተገናኝተው ጨዋታው በመቐለ 4-1 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። የስያሜ ለውጥ ያደረጉት መቐለዎች ጅማን ለቻምፒዮንነት ያበቁት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን በማምጣት እና አስራ አንድ ተጫዋቾችን በማስፈረም ወደ አዲሱ የውድድር ዓመት ገብተዋል። በበርካታ ለውጦች ውስጥ ለማለፍ የተገደደው ደደቢት ከብዙሀኑ ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቶ እና ወጣቶች ላይ የተመሰረተ ቡድን ይዞ የሚቀጥል ይሆናል። አሰልጣኝ ጌቱ ተሽመ እና ኤልያስ ከአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ህልፈት በኋላ የተረከቡትን ኃላፊነት ይዘው ቀጥለዋል። መቐለ ስታድየም ላይ በሚደረገው ጨዋታ ከመስመር የአማካይ ክፍሉ በፍጥነት ኳሶችን ወደ አጥቂዎቹ ለማድረስ የሚጥር መቐለን እና በአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክር ደደቢትን እንደሚያስመለክተን ይገመታል።
ስዩም ተስፋዬ ፣ አቼምፖንግ አሞስ እና ያሬድ ከበደ በመቐለ በኩል ጉዳት ያስተናገዱ ተጫዋቾች ሲሆኑ ደደቢት የአብስራ ተስፋዬ ከጉዳት ተመልሶለታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ቡድኖቹ አምና በሁለቱ ዙሮች አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል ደደቢት ሦስት ግቦች መቐለ ደግሞ ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል።
– ሁለቱም ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ በተጫወተው ቡድን አሸናፊነት የተጠናቀቁ ነበሩ። ደደቢት መቐለ ላይ 2-0 ሲያሸንፍ መቐለ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ 2-1 ረቶ ነበር።
ዳኛ
– ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንዲመራ የተመደበው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ነው።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)
ፍሊፔ ኦቮኖ
ዮናስ ግርማይ – አሌክስ ተሰማ – ቢታድግልኝ ኤልያስ – አንተነህ ገብረክርስቶስ
ሐይደር ሸረፋ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ሳሙኤል ሳሊሶ
ዓርአዶም ገ/ህይወት – አማኑኤል ገብረሚካኤል
ደደቢት (4-3-3)
ረሺድ ማታውሲ
ዳግም አባይ – ኤፍሬም ጌታቸው – ዳዊት ወርቁ – ኄኖክ መርሹ
አቤል እንዳለ- ዓለምአንተ ካሳ – የአብስራ ተስፋዬ
መድኃኔ ብርሀኔ – ዳንኤል ጌዲዮን – እንዳለ ከበደ
ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ |
የአዲስ አበባ ስታድየም በመጀመሪያ የዓመቱ ጨዋታው በ10፡00 ኢትዮጵያ ቡናን እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኛል። ከበርካታ ተጫዋቾቻቸው ጋር መለያየታቸው የሚያመሳስላቸው ሁለቱ ቡድኖች በአሰልጣኝ ለውጥ ላይ ግን ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ከፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ጋር አብሮ ቀጥሏል። ቀደም ብለው የዝግጅት ጊዜያቸውን የጀመሩት ቡናማዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን በማንሳትም ነው ለሊጉ ጅማሮ የደረሱት። በትግራይ ዋንጫ እስከ ፍፃሜ የተጓዙት ድሬዎች በበኩላቸው የአሰልጣኝ ቡድናቸውን አሸጋሽገው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ሾመዋል። በተለይም ከወገብ በታች ያሉ ተጫዋቾቻቸውን ውል አራዝመው በርካታ ዝውውሮችን በመፈፀምም ለነገው ጨዋታ ደርሰዋል። በነገው ጨዋታ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው እንደሚያጠቁ ድሬዎች ደግሞ በጠንካራ የመከላከል መሰረት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመፍጠር ላይ እንደሚያተኩሩ ይጠበቃል።
በጨዋታው አማኑኤል ዮሃንስ ከኢትዮጵያ ቡና በረከት ሳሙኤል ከድሬዳዋ ከተማ በጉዳት የማይኖሩ ተጫዋቾች ናቸው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– በሊጉ የ14 ጊዜ ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና 7 ጊዜ ሲያሸንፍ 5 ጊዜ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ ከተማ 2 ጊዜ አሸንፈዋል። ቡና 23 ፣ ድሬዳዋ 12 ጎል አስቆጥረዋል።
– አዲስ አበባ ላይ ላይ 7 ጊዜ ተገናኝተው ቡና አራቱን ሲያሸንፍ ሦስት ጊዜ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ አሸንፎ አያውቅም። ከሦስቱ አቻ ውጤቶች ሁለቱ ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት የተመዘገቡ ናቸው።
– አምና በሁለተኛው ዙር ያለግብ የተጠናቀቀው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከዋንጫ ፉክክሩ ያስወጣ የድሬዳዋን በሊጉ የመቆየት ተስፋ ያለመለመ ነበር።
ዳኛ
– ፌደራል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አህመድ ረሺድ – ቶማስ ስምረቱ – ክሪዝስቶም ንታንቢ – ተካልኝ ደጀኔ
ሳምሶን ጥላሁን – ዳንኤል ደምሴ – ካሉሻ አልሀሰን
አስራት ቱንጆ – ሎክዋ ሱሌይማን – አቡበከር ነስሩ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ሳምሶን አሰፋ
ሚኪያስ ግርማ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ወሰኑ ማዜ
ፍሬድ ሙሺንዲ – ምንያህል ይመር
ሳሙኤል ዮሀንስ – ኢታሙና ኬይሙ – ሰይላ አብዱላሂ
ራምኬል ሎክ