ሪፖርት| ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመኑን በድል ጀምሯል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2011 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲውሉ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና በድሬዳዋ ከተማ ቢፈተንም የኃላ ኃላ 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን በድል ጀምሯል፡፡

10 ሰአት ሲል በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ባሳለፍነው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፍጻሜ ከተቀሙባቸው ተጫዋቾች ውስጥ ፊት መስመር ላይ እንዲሁም በተከላካይ መሰመር ላይ ጉዳት ከገጠማቸው ሱሌይማን ሉኩዋና ቶማስ ስምረቱ ምትክ ሚኪያስ መኮንንና ተመስገን ካስትሮን በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት አመዛኙን የቅድመ ውድድር ጊዜ ከቡድኑ ጋር ያላሰለፉትን ሳምሶን አሰፋንና አንተነህ ተስፋዬን በቋሚ ስብስባቸው ውስጥ አካተው ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡

እምብዛም ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች ባልነበሩበትና ወደ ድሬዳዋ ከተማ የሜዳ ክልል አድሎቶ በተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ነበረው፡፡ በተደራጀ መከላከል አልፎ አልፎ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በ6ኛ ደቂቃ ሀብታሙ ወልዴ እንዲሁም ራምኬል ሎክ ከቅጣት ምት ከሞከሯቸው ኳሶች ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ በነበሩበት በዚሁ አጋማሽ በ18ኛው ደቂቃ አቡበከር ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ የመታውንና ሳሚ በእግሩ ያዳነበት እንዲሁም በ33ተኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ሞክሮት ሳምሶን በተመሳሳይ ያዳነበት ኳስ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በ29ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሳምሶን ጥላሁን በመምታት አስቆጥሮ ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በመጠኑም ቢሆን የተነቃቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል ፤ ነገርግን የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ያገኙትን የቅጣት ምት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች መዘናጋትን ተከትሎ በፍጥነት በማሻማት ኢታሙና ኬይሙኒ ሳይጠበቅ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሮ ሁለቱ ቡድኖች 1ለ1 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ አስችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ በሚያስችል መልኩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት ችሏል፡፡ በ53ኛው ደቂቃ ድሬዳዋ ከተማዎች ዘነበ ከበደ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የሞከራትና የግቡን አግዳሚ ለትማ ከተመለሰችው ኳስ ውጪ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ቢደርሱም የድሬዳዋን የመከላከል አደረጃጀት ለመስበር ረጅም ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡ 84ኛው ደቂቃ ላይ ተካልኝ ደጀኔ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ በድሬዳዋ ሳጥን ውስጥ በነጻ አቋቋም ላይ የነበረው አህመድ ረሺድ በእግሩ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ስትመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አቡበከር ናስር በግንባር በመግጨት ቡድኑን አሸናፊ ያረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ጨዋታው በባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመራው ኢንተርናሽናል አርቢቴር አማኑኤል ኃይለስላሴ ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶች መዘዋል። 


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ | LINK



ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ