ዳሽን ቢራ የአርሰናል ይፋዊ አጋር ድርጅት ሆነ

 

ዳሽን ቢራ አክሲዮን ማህበር የእንግሊዙ ክለብ አርሰናል ይፋዊ አጋር የሚያደርገውን ውል መፈራረሙን ዛሬ አስታውቋል። ድርጅቱ ዛሬ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ውሉ ለቀጣይ 3 ዓመታት የሚዘልቅ እንደሆነ ገልጿል።

የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቭሊን ሄይንስወርዝ እንደተናገሩት ይህ ፈር ቀዳጅ ስምምነት ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

እንደምታውቁት በቀጣይ ሳምንታት በደብረብርሃን የገነባነው አዲስ ፋብሪካ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ምርት የሚገባ ይሆናል። ይህን የዳሽን ቢራ ብሩህ ጉዞ በማስመልከት እንግሊዛውያኑ የድርጅታችን ሼር ሆልደሮች ዱቬት እና ቫሳሪ ከአርሰናል ክለብ ጋር ባላቸው ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ይህንን የትብብር ስምምነት አመቻችተዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ዳሽን ለቀጣይ 3 ዓመታት የአርሰናል ይፋዊ የቢራ ስፖንሰር መሆኑን እንገልፃለን።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል። በአመት ለበርካታ ጊዜያት የአርሰናል አሠልጣኞች እና የክለቡ የቀድሞ ዝነኛ ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከፌዴሬሽኑ ጋር በትብብር ለኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች ስልጠና እንዲሰጡ ይደረጋል። የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ለኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች በቅርበት ማምጣቱ ሌላው የስምምነቱ ጠቀሜታ ነው። ዳሽን የተለያዩ የማስተዋወቂያ ጥቅሎችን ለደንበኞቹ የሚያቀርብ ይሆናል።

ዴቭሊን ሄይንስወርዝ አያይዘውም አዲሱ ስምምነት ድርጅቱንና ደንበኞቹን ይበልጥ የሚያቀራርብ መሆኑንም ገልፀዋል።

አላማችን ደንበኛዎቻችንን ማስደሰት ነው። ከአርሰናል ጋር ያለን አጋርነት ዳሽንን ከደንበኞቹ እና ከቢራ ተጠቃሚዎች ጋር ይበልጥ የሚያቀራርብ ነው። ስምምነቱ ዳሽንንም፣ አርሰናልንም፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስን ተጠቃሚ ያደርጋል።

IMG_1616

በኢትዮጵያ የብሪታንያ አምባሳደር ግሬግ ዶሬይ በበኩላቸው ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በብሪታንያ መሃል ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያና ብሪታንያ በኢኮኖሚ ድጋፍ፣ በንግድ፣ በቀጠናው የፀጥታ ጉዳይ እና እንደ የአለም ሙቀት መጨመር ባሉ ዓለምዓቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ። የስፖርት ዲፕሎማሲ ወሳኝ የሆነ የስራችን አካል ነው። ከረጅም ጊዜ በፊትም በኢትዮጵያውያን ያለውን የስፖርቱ ፍቅር ለመመልከት ችለናል። ዳሽን በግሌ ከምወዳቸው የኢትዮጵያ ቢራዎች ውስጥ አንዱ ነው። ስለዚህ ከአርሰናል ጋር በተፈራረሙት ስምምነት እጅግ ደስተኛ ሆኛለሁ።

የአርሰናል ክለብ የንግድ ጉዳዮች ሃላፊ ቪናይ ቬንካቴሻም ለክለባቸው ድረ-ገፅ እንደገለፁት ከዳሽን ጋራ የሚኖረው ትብብር አርሰናልን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ደጋፊዎቹ ጋር የሚያቀራርብ እንደሆነና ዳሽን በሚሰራቸው ማህበረሰብ ተኮር ስራዎች ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።

አርሰናል በአፍሪካ ትልቅ የደጋፊ መሰረት አለው፤ በኢትዮጵያ ያለን ድጋፍ ደግሞ ላቅ ብሎ የሚታይ ነው። ከዳሽን ጋር የፈጠርነው አጋርነት ክለባችንን ወደዚህ በፍጥነት እያደገ ወደሚገኝ ክልል የሚወስድ በመሆኑ ደስተኛ ነን።

ይህ ፈርቀዳጅ ስምምነት አርሰናል እግርኳስ ክለብን በኢትዮጵያ ካለ ድርጅት ጋር በትብብር በመስራት የመጀመሪያው እና ብቸኛው የእንግሊዝ ፕሪምየር ክለብ ያደርገዋል።

ያጋሩ