የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ዛሬ ሲቀጥል አዳማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር አዳማ ከተማን 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
አምና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻው የመዝጊያ ጨዋታ ላይ የተገናኙት አዳማ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር በ2011 የውድድር ዘመን ደግሞ በመጀመርያው ሳምንት ላይ ሊገናኙ ችለዋል። ጨዋታውን ከመሩት ዳኞች አመራር አንስቶ በሜዳ ላይ የተሳተፉትን ተጫዋቾች እና ተመልካቹ ጨምሮ ፍጹም በስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ተጠናቋል።
ሁለቱ ክለቦች በአዳዲስ አሰልጣኞች የሚመሩ ቢሆንም የጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝ ዘማርያም የአንድ ዓመት ቅጣታቸውን ባለመፈፀማቸው ከተመልካች ጋር በመቀመጥ በስልክ ለረዳቶቻቸው በመንገር ቡድኑን ሲመሩ ታይተዋል። አዳማ ከተማ አዲስ ፈራሚዎችን በተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጦ የመጀመርያ አስራ አንዱ በሙሉ ዓምና ከቡድኑ ጋር የነበሩ ሲሆኑ በአንፃሩ አባ ጅፋር ከአምና ስብስቡ ዳንኤል አጄይ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ አዳማ ሲሶኮ እና ይሁን እንደሻው ብቻ ሲጠቀም የተቀሩት አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች ነበሩ።
የጨዋታው የመጀመርያ 10 ደቂቃ ብዙም ያልተደራጀ እና ያልተረጋጋ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች ብንመለከትም ጨዋታው እየጋለ ሄዶ አባ ጅፋሮች በዲዲዬ ለብሪ ከሳጥን ውጭ የግብ ጠባቂውን ጃኮን አቋቋም አይቶ ቺፕ በማድረግ የመታው ኳስ ጃኮ እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። የጨዋታውን እንቅስቃሴ መቀየር የሚችል አጋጣሚ ቡልቻ ሹራ ብቻውን ከመሀል ሜዳ አንስቶ እየገፈ በመሄድ ጎል አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ከጨዋታው አቋቋም ውጭ ለነበረው ዳዋ ሆቴሳ አቀብሎት ዳዋ ወደ ጎልነት ቢቀይረውም ዳኛው ዳዋከጨዋታ ውጭ አቋቋም በመሆኑ ጎሉ ሳይፀድቅ ቀርቷል።
ጨዋታው በተደጋጋሚ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ጎል በመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች በሁለቱም ቡድኖች መመልከት ብንችልም መጨረሻው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በሚበላሹ ኳሶች ምክንያት ጎል መመልከት ሳንችል የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ በሰባት ደቂቃ ውስጥ ተቀይሮ እስከወጣበት ድረስ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ እና የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው መስዑድ መሐመድ ለአስቻለው ግርማ አቀብሎት አስቻለው በ47ኛው ደቂቃ ጅማዎችን ቀዳሚ ማድረግ ሲችል ብዙም ሳይቆይ 52ኛው ደቂቃ ከአስቻለው ግርማ ከቀኝ መስመር በጥሩ መንገድ ያሻገረለትን መስዑድ መሐመድ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የጎል መጠኑን ሁለት ማድረግ ችሏል።
ጅማዎች በፍጥነት ሁለት ጎሎች ማስቆጠራቸው በራስ መተማመናቸውን ከፍ አድርጎላቸው ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረው ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ሲሳካላቸው በአንፃሩ አዳማዎች ያልተሳካ እና በተመልካቹ ዘንድ ተቃውሞ ያስነሳው የአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም የተጫዋቾች ቅያሪ ብዙም ሳይፈይድላቸው መጨረሻው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጭ የሞከረው እና የግቡ አግዳሚ ከመለሰበት ሙከራ ውጭ ሌላ ሊጠቀስ የሚችል ሙከራ ሳናይ ጨዋታው በእንግዳው ጅማ አባ ጅፋር 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጨዋታው በዚህ መልኩ በጅማ አባጅፋር አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ጨዋታውን የመሩት ፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው አንድም የማስጠንቀቂያ ካርድ ሳይመዙ ተጠናቋል።
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይህን ይጫኑ | LINK |
ማስታወቂያ |
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ |