አዳማ ከተማ 0-2 ጅማ አባ ጅፋር | የአሰልጣኞች አስተያየት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ የአምናው ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጪ አዳማ ከተማን 2-0 በማሸነፍ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን በድል መጀመር ችሏል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ ብለናል።

” ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀማችን አሸንፈን እንድንወጣ አስችሎናል።” የጅማ አባ ጅፋር ም/አሰልጣኝ ዩሱፍ ዓሊ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነው፤ ማሸነፍ ይገባናል። ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ለመውጣት የምንችለውን አድርገናል። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅመን መውጣታችን አሸንፈን እንድንወጣ አስችሎናል።

አዲስ አበባ ሲቲ ካፕ መካፈላቸው…

የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ መሳተፋችን በጣም ጠቅሞናል። ቡድናችን እንደምታዩት አዲስ ነው፤ ስለዚህ ቡድኑን ለመስራት እና እንዲቀናጁ ለማድረግ ሲቲ ካፑ ላይ መሳተፋችን በጣም ጠቀሜታ አለው።

የአምናው ቻምፒዮንነት ይደገማል?

የአምናው ቡድናችን በፍላጎት በመጫወት የተሻለ ቡድን ነው። ይህ ቡድን አብዛኛዎቹ የቡና ተጫዋቾች ናቸው። ኳስ ይዘው የሚጫወቱ መሆናቸው እነሱን ለማደራጀት ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም። ከዚህ በኋላም ጠንክረን ሰርተን ዓምና ውጤት ብቻ ነው። ዘንድሮ ኳሱንም ውጤቱንም አስጠብቀን የአምናውን ክብር እንደግማለን።


“እነሱ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዋል፤ እኛ አልተጠቀምንም።” አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነው። የመጀመርያው አጋማሽ የተሻልን ነበርን። የጎል ዕድል መፍጠር ችለን ነበር አልተጠቀምንበትም እንጂ ከሞላ ጎደል ጨዋታው ጥሩ ነው። እነሱ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዋል፤ እኛ አልተጠቀምንም። ይሄ ነበር ጨዋታው።

የመጀመርያ ሽንፈት ሜዳው ላይ መሆኑ…

እግርኳስ ነው ምንም ችግር የለውም። የመጀመርያ ጨዋታ ነው፤ ገና 29 ጨዋታ ይቀራል። እኛም ከሜዳ ውጭ እናሸንፋለን። ዛሬ የተከላካዮቻችን የአቋቋም ስህተት ነው ዋጋ ያስከፈለን፤ በቀጣይ እያስተካከልን እንሄዳለን። እንዲያውም ሽንፈቱ መጀመርያ መሆኑ ከዚህ በኋላ ጠንክረህ እንድንሰራ ያደርገናል። ክፍተታችንን እንድናርምና ስህተቶቻንን የት ጋር እንደሆኑ ለማየት ያስችለናል።

የተጫዋች ቅያሪ…

ሽንፈት ሁለትም ባዶ አንድም ባዶ አንድ ነው። እነሱን (ሱሌይማን እና ተስፋዬን) መቀየሬ መቀየሬ የአጥቂነት ባህሪ ያላቸውን ልጆች በማስገባት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲሆን በዚህም አራት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን እንድንፈጥር አድርጎናል ።

ቀጣይ ጨዋታ ( ከጊዮርጊስ )

አዎ የ15 ቀናት ጊዜ አለን። በቀጣይ የምንሰራቸው ስራዎች እንድንሰራ ጊዜው መራቁ የሚያግዘን ይሆናል ።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ