በ1938 የተመሰረተውና በህልውናው የቀጠለ 2ኛው የሃገራችን አንጋፋ ክለብ የሆነው መከላከያ ይህንን ጨዋታ ካሸነፈ 13ኛ የኢትዮጵያ ዋንጫ ድሉ ይሆናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን በ3 ዋንጫዎች በመብለጥም በርካታ ዋንጫ በማንሳት መምራቱን ይቀጥላል፡፡

ጦሩ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው መከላከያ በኢትዮጵያ ዋንጫ ስኬታማ አመታትን ያሳለፈው በ1940ዎቹ ነው፡፡ መከላከያ ካገኛቸው 12 ዋንጫዎች ከግማሽ በላዩን (7) ያገኘው ከ1938-1948 ባሉት አመታት ነው፡፡ በ1967 ፣ 1974 ፣ 1982 ፣ 1998 እና 2005 ሌሎች ዋንጫ ያገኘባቸው ዘመናት ናቸው፡፡ መከላከያ ጦር ሰራዊት (ከ1938 እስከ 1946) በሚል ስያሜው 5 ጊዜ ፣ መቻል(1947-1977) በሚል መጠርያው 4 ጊዜ ፣ ምድር ጦር በሚል ስያሜ (1978-1983) 1 ጊዜ ፣ በአሁኑ መጠርያው መከላከያ ደግሞ 2 ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡ መከላከያ ለ3 ተከታታይ አመታት ይህንን ዋንጫ በማንሳት ብቸኛው ነው፡፡

ጦሩ በ2 አጋጣሚዎች ለ3 ተከታታይ አመታት ዋንጫውን አሰንስቷል፡፡ (1941-1943 እና 1946-1948)

ሀዋሳ ከነማ ከመከላከያ ጋር የሚነፃፀር ታሪክ በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ የለውም፡፡ በ1978 የተመሰረተው ሀዋሳ ከነማ በ1997 ኢትዮጵያ ባንኮችን (የአሁኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) አሸንፎ ዋንጫውን ከማንሳቱና በ2000 ፍፃሜ ከመድረሱ ውጪ የሚጠቀስ ታሪክ የለውም፡፡

በ1937 የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫን 22 ክለቦች አሸንፈውታል፡፡ ከነዚህ 22 ክለቦች መካከል አሁን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ እየተወዳደሩ ያሉት 12 ናቸው፡፡ ኤርትራ ጫማ ፣ ክቡር ዘበኛ ፣ ቀይ ባህር ፣ ብሪቲሽ ሚሊተሪ ሚሽን ፣ አስመራ ፣ እርምጃችን ፣ ህንፃ ኮንስትራክሽን ፣ ሀዋሳ ዱቄት ፣ ወላይታ ቱሳ እና ፖሊስፖርቲቫ የኢትዮጵያ ዋንጫ የወሰዱና የፈረሱ አልያም ከኤርትራ መገንጠል በኋላ በኢትዮጵያ መቆየት ያልቻሉ ክለቦች ናቸው፡፡

ከ1937 እስከ 2007 ባሉት 70 አመታት ውስጥ በተለያዩ 14 ጊዜያት ውድድሩ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ከ1953-1961 ፣ 1971 ፣ 1981 ፣ 1983 ፣ 1984 እና 2004 ውድድሮቹ ያልተካሄዱባቸው አመታት ናቸው፡፡

በአጠቃላይ መከላከያ 12 ዋንጫዎች በመሰብሰብ ይመራል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ጊዜ ዋንጫ ሲያነሳ ኢትዮጵያ ቡና 5 ጊዜ ፣ ኤሌክትሪክ 4 ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ ደደቢት ፣ መድን ፣ ቀይ ባህር ፣ ፌዴራል ፖሊስ (ኦሜድላ) ፣ ክበር ዘበኛ እና ኤርትራ ጫማ 2 ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ ሀዋሳ ከነማ ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፣ ሀረር ሲቲ እና ንግድ ባንክ 1 ጊዜ ካነሱት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በዚህ ውድድር ላይ የዋንጫ ባለቤት የሚሆኑ ክለቦች ለአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ያልፋሉ፡፡አንድ ክለብ ፕሪሚየር ሊጉን እና ጥሎ ማለፉን ካሸነፈ በጥሎ ማለፍ 2ኛ የሚወጣው የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎን ያገኛል፡፡ ከዚህ በፊት ይህንን ውድድር ሳያሸንፉ ለአፍሪካ ውድድር ከተካፈሉ ክለቦች መካከል ጉና ንግድ (1991 በጊዮርጊስ ተሸንፎ) ፣ መድን (1993 በኤሌክትሪክ ተሸንፎ) ፣ 2002 ንግድ ባንክ (በጊዮርጊስ ተሸንፎ) በ2004 (ደደቢት (የጥሎ ማለፍ ውድድር ባለመካሄዱና ሊጉን በ2ኝነት በማጠናቀቁ) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ያጋሩ