ከ2007 የውድድር ዘመን አንስቶ ከሦስት ወደ አምስት ከፍ እንዲል የተደረገው በአንድ ቡድን ውስጥ መያዝ የሚቻለው የውጪ ተጫዋቾች ቁጥር ወደ ቀደመው ሦስት ዝቅ ሊል እንደሚችል ተገለፀ።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ዛሬ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከአዲስ አበባ መስተዳድር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በጋራ በመሆን በኢንተርኮንትኔታል አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊዎች “የውጭ ተጫዋቾች ቁጥር እየጨመረ ነው። የውጭ ተጫዋቾች ይምጡ ሆኖም ቁጥሩ ይገደብ፤ ለታዳጊዎች ዕድል ይሰጥልን” በሚል ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “በቀጣይ ቁጥሩ ወደ ሦስት ዝቅ ይላል። በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ከክለቦች ጋር በነበረው ውይይት ይሄን አንስተን ተነጋግረናል። ዘንድሮ ወደ ሦስት ለማድረግ አስበን የነበረ ቢሆንም ክለቦች ተጫዋቾቹ የኮንትራት ውል ያለባቸው በመሆኑ የማፍረሻ ካሳ የመክፈል ግዴታ ውስጥ እንዳይገቡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለማስተካከል እንሰራለን።” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በጥቂት ተጫዋቾች የተጀመረው የውጪ ተጫዋቾች የማስፈረም ልማድ አሁን ላይ ተንሰራፍቶ አመዛኞቹ ክለቦች ህጉ የሚፈቅድላቸው የአምስት ተጫዋቾችን ቦታ ሲሸፍኑ እየታየ ነው። ይህም ለአዳዲስ ተጫዋቾች የሚሰጠውን እድል እንዲቀንስና በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ጉዞ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አድርጎታል ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ይሰጣሉ።