የአበባው ቡታቆ ጉዳይ

ለአርባምንጭ ከነማ ለመጫወት ከስምምነት ደርሶ የነበረው አበባው ቡታቆ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደሚመለስ ክለቡ ማሳወቁን ተከትሎ የመነጋገርያ ርእስ ሆኗል፡፡ ግራ መስመር ተከላካዩ ከአርባምንጭ ጋር በወር 79ሺህ ብር እንዲከፈለው ተስማምቶ ክለቡን የተቀላቀለ ሲሆን በቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይም ተሳታፊ ነበር፡፡ ወላይታ ድቻን ባሸነፉበት የዝግጅት ጨዋታም ግብ አስቆጥሮ ነበር፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ህዝብ ግንኙነት አቶ ኤርሚስ አሽኔ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገረው ተጫዋቹ ለአርባምንጭ በይፋ ባለመፈረሙ ወደ ክለባቸው እንዲመጣ አድርገዋል፡፡ ‹‹ ከአበባው ጋር በገንዘብ ደረጃ ምንም ድርድር አላደረገም፡፡ ዛሬ ልምምድ እንዲጀምር ብቻ ነው የተነገረው፡፡ አሰልጣኙ ተጨማሪ የግራ መስመር ተከላካይ እንደሚፈልጉ በመናገራቸው የነበረን አማራጭ እሱ ነበር፡፡ ከአርባምንጭ ጋር ስላለው ውል የምናውቀው ነገር የለም፡፡ፌዴሬሽን እስካልፈረመ ድረስ የኔ ነው ሊሉ አይችሉም፡፡ በስልክ ባደረግነው ግንኙነት ከጊዮርጊስ ውጪ ለሌላ ክለብ መጫወት እንደማይፈልግ ሲነግረን ቆይቷል፡፡›› ብለዋል፡፡

የአርባንምጭ ከነማ ጊዜያዊ አሰልጣኝ መለሰ ሸመና በበኩላቸው ስለ ጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ እስከማውቀው ድረስ አበባው ከኛ ጋር ልምምድ እያደረገ ነበር፡፡ ከክለቡ አመራሮች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ነው የማውቀው፡፡ አበባው እና ታደለ የጠየቁት ገንዘብ እስካሁን ስላልተከፈላቸው እየተደራደሩ መሆኑን ነው የማውቀው፡፡ ›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአበባው ቡታቆን ውል የሚገልፅ ምንም አይነት ፋይል ከክለቦቹ እንዳልተላከለት ከፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ውል አለን የሚሉ ከሆነ ለፌዴሬሽኑ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው ተብሏል፡፡
ያጋሩ