አስተያየት | በዘርዓይ ኢያሱ |
አዲስ አሰልጣኝ ወደ አዲስ ክለብ ሲመጣ አዲስ የጨዋታ አስተሳሰብ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መገመት የተለመደና ወደፊትም ሊኖር የሚችል ነው፡፡ አዲሱን አስተሳሰብ ተከትሎ የአሰልጣኙን ስራ መተቸትና ማመስገን ደግሞ ቀጥሎ የሚመጣ ነገር ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ እጣ ፈንታ ከገጠማቸው አሰልጣኞች መካከል የቀድሞው (ሰሞኑን የተሰናበቱት) የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ካርሎስ ማኑኤል ቫስ ፒንቶ ናቸው፡፡
ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ባለፈው የውድድር ዓመት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታቸውን ያደረጉት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ነበር፡፡ በወቅቱ አሰልጣኙ ይዘውት የቀረቡት ቡድን ክለቡ ከሚታወቅበት ጨዋታ ዘይቤ ወጣ ያለና ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወት ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ ክለቡ አዲስ በተባለው አቀራረብ እንዴት ያለፉትን ስኬቶች ሊያስቀጥል ይችላል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም፡፡ ነገር ግን ሰውዬው በክለቡ ብዙም የማይዘወተረውን የጨዋታ አቀራረብ ተከትለው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እስከ ፍፃሜ ተጉዘው ሻምፒዮን ሆኑ፡፡
ይህ ስኬት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣይ መንገድ ምን ሊሆን እንደሚችል ያሳየ ሲሆን የአሰልጣኙንና የተጨዋቾቹን በራስ መተማመን ከፍ አድርጎታል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ በቫስ ፒንቶ ላይ ጥያቄ ያነሱ ወገኖች ከአስተያየታቸው እንዲቆጠቡ አድርጓል፡፡ ከዚያም ጥያቄው ጋብ አለና በፕሪምየር ሊጉ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችል ለማየት ቀጥሮ ይዘን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ወደ ኢትዮጵያ በመጡ በመጀመሪያው ዓመት ማንሳታቸውን አድንቀን ተለያየን፡፡
የፒንቶ ውድቀት
እርግጥ ነው የቫስ ፒንቶ ቡድን ብዙ ጨዋታዎችን የተሸነፈ አይደለም፡፡ በሊጉ በሶስት ጨዋታዎች ብቻ መሸነፉ ለዚህ ምስክር ከመሆኑ በተጨማሪ ባለፈው የውድድር ዓመት ትንሽ ጨዋታ የተሸነፈ ብቸኛው ቡድን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከ2009 ዓ.ም የተሻለ ሪከርድ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ግን ደግሞ ከ30 ጨዋታዎች ያሸነፉት 14 ብቻ መሆኑን ስንመለከት ከ2009 የውድድር ዓመት በ14 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ ይህ ማለት የማሸነፍ ንፃሬያቸው በመቶኛ ሲለካ 46.7 በመቶ ሲሆን ግማሹን እንኳን ማሸነፍ አልቻሉም፡፡
በሌላ አገላለፅ 23 በመቶ አቻ 10 በመቶ ተሸንፏል ማለት ነው፡፡ ይህ አሃዝ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሻምፒዮን አላደረገውም፡፡ ለፒንቶም ተጨማሪ እድል አላሰጣቸውም፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ውድድር ለመሳተፍ ብቸኛው ተስፋው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት ነበር፡፡ በዚህም ቢሆን አልተሳካም፡፡ በፍፃሜው በመከላከያ ተረተው ብቸኛውን ተስፋቸውን አሳልፈው ሰጡ፡፡ ይህ በመሆኑ የመጀመሪያ ተጠያቂ አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ ሲሆኑ ወንበራቸው ይበልጥ መነቃነቅ የጀመረው በመከላከያ ያገጠማቸው ሽንፈት ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
የፒንቶ እሮሮ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤት እያጣ ሲመጣ 4-3-3 ፎርሜሽን መጠቀማቸው የችግሩ መሰረት ስለመሆኑ በጭምጭምታ መወራት ጀመረ፡፡ ይህ ስር የሌለው ወሬ አሰልጣኙ ጋር ደርሶ ነበርና የቡድኑ ችግር 4-3-3 ፎርሜሽን ሳይሆን ሁነኛ አጥቂ ማጣት እንደሆነ ተናገሩ፡፡ በተለይ ደግሞ የሳላሃዲን ሰዒድ በጉዳት ከቡድኑ መራቅ ዋነኛ ችግር አድርገው ሲያነሱ ቆይቷል፡፡ በርግጥም እዚህ ጋር እውነት አላቸው፡፡ ሳላሂድን በአመት 15 እና ከዚያ በላይ ጎሎችን ማስቆጠር የሚችል የትኛውም አሰልጣኝ የኔ በሆነ የሚለው አጥቂ ነው፡፡ የሃገሪቱ ሊጎች የአጥቂ ድርቅ ያለባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሰልጣኙ የሳላሃዲን አለመኖር እንደጎዳቸው ቢናገሩ እንደ አንድ ምክንያት ቢነሳ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡
ነገር ግን እንዲህ አይነት አጣብቂኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለችግርሩ እልባ ለመስጠት ከሁሉም ቀዳሚ መሆን ያለባቸው አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ለዚህም እጃቸው ላይ ያለውን የሰው ሃይል መነሻ በማድረግ ጠንከር ያሉና ያልተለመዱ ውሳኔዎችን መወሰን ይኖርባቸዋል፡፡ ውሳኔዎቹም በአመዛኙ ታክቲካዊ ሊሆን ይችላል፡፡
ለምሳሌ በታክቲክ እውቀት የበለፀጉ ታላላቅ አሰልጣኞች እንዲህ አይነት ፈተና በሚያገጥማቸው ግዜ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮቻቸውና የመስመር አጥቂዎቻቸው ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ስትራቴጂ ይነድፋሉ፡፡ እንዲህ በማድረጋቸው ዘላቂ ባይሆንም ግዚያዊ መፍትሄ ማግኘት የቻሉ አሰልጣኞች ቁጥር ብዙ ነው፡፡
ፒንቶ ግን ያሉትን ተጨዋች ያማከለ አማራጭ የጨዋታ ስልት አላዘጋጁም፡፡ የማጥቃትንና የመከላከል ስትራቴጂያቸው ላይ ለውጥ አላደረጉም፡፡ ይህን ዓይነት አማራጭ ከመውሰድ ይልቅ በአጥቂ ስፍራ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አዳነ ግርማንና አሜ መሃመድን እያፈራረቁ ማጫወት መርጠዋል፡፡ መፍትሄ ግን አላገኙበትም፡፡ ቡድኑ ውጤት ሲርቀውም ሆነ ሲሳካለት ከዚያው ከ4-3-3 ሊላቀቁ አልቻሉም፡፡
የተጨዋች አጠቃቀም ክፍተቶች
አንድ አሰልጣኝ ቋሚ ተሳለፊዎችን የመምረጥ ሙሉ ስልጣን አለው፡፡ ውጤት እየራቀው ሲመጣ ደግሞ ለምን የሚል ጥያቄ ሲነሳበት አሳማኝ የሆነ ምክንያት የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱን ማስረዳት ካቻለ ደግሞ የሚሰራው በግምት ነው ወደ ሚለው ድምዳሜ ያርሳል፡፡ በ2009 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን ቡድኑ እንደ ቡድን ያበረከተው አስተዋፅኦ እንዳለ ሆኖ የግለሰቦች ወቅታዊ ብቃት ጉልህ ድርሻ ነበረው፡፡ ለዚህም እንደ አብነት ልጠቅስ የምችለው የመስመር አጥቂውን በሃይሉ አሰፋ (ቱሳን) ነው፡፡ በወቅቱ በሃይሉ በምርጥ ብቃት ላይ ከመገኙቱ በተጨማሪ ከእሱ የሚነሱ ኳሶች ነበሩ በተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ አደጋ እየፈጠሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ሲያስቆጥር የነበረው፡፡
ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ፒንቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተረከቡ በኋላ በኃይሉ አሰፋን በቋሚ አሰላፍ ውስጥ ያየንበት አጋጣሚ በጣም ጥቂት ነበር፡፡ ተጨዋቹ ከደደቢት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተዘዋረበት ግዜ ጀምሮ ቁልፍ ከሚባሉ ተጨዋቾች ተርታ ይሰለፍ ነበርና ለምን የመጫወት እድል በደንብ አልተሠጠውም የሚል ጥያቄ ቢነሳ አያስደንቅም፡፡
ነገር ግን ከእሱ ይልቅ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ያልተሳካ ግዜ ያሳለፈው ኢብራሂማ ፎፋና በአሰልጣኙ ተመራጭ ነበር፡፡ ይህ ተጨዋች ምንም እንኳ በቋሚነት ለመጫወት በአሰልጣኙ እምነት ቢያገኝም የበኃይሉን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር አለመቻሉን ተመልክተናል፡፡ ተጫዋቹ ጎል ማግባቱና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበሉ ቀርቶ ከቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሃመድ ጋር ተግባብቶ መጫወት አለመቻሉ የቡድኑ ትልቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
አብዱልከሪም በማጥቃት ለመሳተፍ ከእሱ ትይዩ መስመር በአጥቂነት ከሚጫወተው ተጨዋች የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ የመስመር አጥቂው ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ወደ 16፡50ው እንዲገባለት ይፈልጋል፡፡
ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ የተጋጣሚ ተከላካዮች በተለይ የግራ መስመር ተከላካዩ አጥቂውን ተከትሎ ወደ 16፤50 የሚገባ በመሆኑ አብዱልከሪም ኮሊደሩን በነፃነት እንዲጠቀም ያስችለዋል፡፡ ለጎል የሚሆኑ የአየር ላይ ኳስ መጠቀም ለሚችሉት ለእነ አዳነ ግርማ ያሻማል፡፡
በኃይሉ ይህን በማድረጉ በኩል ከፎፎና በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀኙ የሜዳ ክፍል ሲያጠቃ እጅግ አስፈሪ የነበረው፡፡ ኢብራሂማ ፎፋና ከመጣ ወዲህ ግን የአብዱልከሪም የማጥቃት ተሳትፎው ቀንሷል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ፎፋና የተጋጣሚዎቹን ተከላካዮች መደበኛ ቦታ የማስለቀቅ ክህሎቱ አነስተኛ በመሆኑ ሲሆን አብዱልከሪም ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ሄዶ ማጥቃት የሚችልበትን ክፍተት እንዳያገኝ አግዶታል፡፡
በመሆኑም አብዱልከሪም በመከላከል ስራ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ተገዷል፡፡ ፎፎና ደግሞ በመከላከሉ በኩል ተሳትፎው በጣም ደካማ በመሆኑ አብዱልከሪም አልፎ አልፎ የምትገኘውን ክፍት ቦታ ለመጠቀም ድፍረቱን ሲያጣ ታዝበናል፡፡
ስለሆነም የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ስልቱ በቀኙ የሜዳ ክፍል እንደመሆኑ መጠን እንዲህ አይነቱ ክፍተት ለቡድኑ ውጤት ማጣት ምክንያት ሆኗል፡፡ ፎፋና ከክለቡ ጋር እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ መዝለቅ ያልቻበት አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል፡፡
ማጠቃለያ
ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚሰለጥን ማንኛውም አሰልጣኝ እስከ ዛሬ ያላሳካቸውን ድሎች ማግኘት ባይችልበ እንኳን የተለመደውን ማስቀጠል ከእሱ የሚጠበቅ መሆኑን ሊረዳ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አዲስ ታሪክ መፃፍ ይቅርና የተለመደውንም ማስቀጠል ባለመቻላቸው ክለቡን እንዲለቁ መደረጉ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2010 ዓመት ሁለት ዋንጫችን ከማጣቱም ባሻገር ከረጅም ዓመት በኋላ በአፍሪካ መድረክ መሳተፍ አይችልም፡፡ ይህም ደግሞ በውጤት ልኬት ለክለቡ መጥፎ ከሚባሉት ግዜያት መካከል ቀዳሚ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል፡፡
*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጋር የተያያዙ አስተያየት አዘል ጽሁፎችን ድረ-ገጻችን ላይ እንደምናስተናግድ እየገለጽን በኢሜይል አድራሻችን abgmariam21@gmail.com ልታጋሩን ትችላላችሁ፡፡ |