ክረምቱን በብዙ ውዝግብ ውስጥ አሳልፎ የነበረው ፌዴራል ፖሊስ በአዲሱ ፎርማት በከፍተኛ ሊግ መቆየቱን ተከትሎ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል።
በ2010 የከፍተኛ ሊግ 30ኛ ሳምንት የተጫዋች ተገቢነት ክስ አስመዝግቦ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወሰነው ውሳኔ ደስተኛ ያልነበረው ፌዴራል ፖሊስ ወደ አንደኛ ሊግ ወርዶ ከመጫወት የሚያድነው ዕድል ተፈጥሮለታል። ትናንት በከፍተኛ ሊግ ላይ በተደረጉ ለውጦች የተሳታፊዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው ፌደራል ፖሊስ ወደ ሦስተኛው የሊግ ዕረከን ከመውረድ የተረፈው። በመሆኑም ክለቡ በተመደበበት የማዕከላዊ ምድብ ውድድሩን እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ክለቡ በከፍተኛ ሊግ የሚያስቀጥለው ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ራሱን ለማጠናከር የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በአሰልጣኝ ቅጥር ጀምሯል። ምርጫው ያደረገው ደግሞ አሰልጣኝ መሣይ በየነን ነው። በሙያው የ16 ዓመታት ቆይታ ያላቸው አሰልጣኝ መሣይ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን በተለያዩ ጊዜያት ያሰለጥኑ ሲሆን ከአንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ጋር በኢትዮጽያ መድን በምክትልነት አብረው ሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሰበታ ሁለተኛ ቡድን ፣ በቡታጅራ ከተማ ፣ በጅማ ከተማ ፣ በነቀምት ከተማ እና በ2010 ደግሞ በዱከም ቆይታ ነበራቸው። አሰልጣኝ መሣይ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከአዲሱ ክለባቸው ፌደራል ፖሊስ ጋር በተፈራረሙት የአንድ ዓመት ውል መሰረት ስራቸውን የሚጀምሩ ይሆናል።